የኢዜማ የባስኬቶ ወረዳ የስራ አስፈጻሚ አባል ታሰሩ

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል በባስኬቶ ልዩ ወረዳ በትላንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሁለት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት መካከል አንዱ አሁንም በእስር ላይ መሆናቸውን ፓርቲው ገለጸ። ግለሰቡ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጠው የልዩ ወረዳው ፖሊስ፤ ሆኖም የተያዙበት ምክንያት ከፓርቲ ስራቸው ጋር በተያያዘ አይደለም ሲል አስተባብሏል። 

ትላንት እሁድ ግንቦት 8 በፖሊስ የተያዙት የኢዜማ አባላት፤ በባስኬቶ ልዩ ወረዳ የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጎዳና ማናዬ እና የስራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ አለማየሁ አያቶ መሆናቸውን የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ጎዳና ትላንትናውኑ መፈታታቸውን የገለጹት የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊው፤ የስራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ አለማየሁ ግን አሁንም በባስኬቶ ልዩ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደሚገኙ አክለዋል። 

የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ከታሳሪዎቹ መካከል የስራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ አለማየሁ አያቶ አሁንም በባስኬቶ ልዩ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል | ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ

ሁለቱ አባላት የታሰሩት በልዩ ወረዳው ዶክ ጫሬ ቀበሌ፤ የኢዜማን ፖሊሲ የማስተዋወቅ እና የምረጡኝ ቅስቀሳ እያከናወኑ በነበሩበት ሰዓት እንደነበር የወረዳው የኢዜማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ሁለቱን ግለሰቦች ትላንት እሁድ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የባስኬቶ ልዩ ወረዳ የፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አለም አጎናፍር፤ የእስራቸው ምክንያት በፓርቲው ከተገለጸው የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።   

“ሰዎቹ  የታሰሩት ከኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ብድር ጋር በተያያዘ፤ በቀበሌው በቁጥጥር ስር የዋለ አንድ ግለሰብ ‘ከእስር መፈታት አለበት’ በሚል ቀበሌውን በማወካቸው ነው” ሲሉ ኢንስፔክተሩ ከኢዜማ አባላቱ እስር ጀርባ አለ ያሉትን ምክንያት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

ሁለቱ የኢዜማ አባላት “ከእስር እንዲፈታ ተሟግተውለታል” የተባለው ግለሰብ በአሁኑ ወቅት ታስሮ የሚገኘው በዶክ ጫሬ ቀበሌ እንደሆነና ከእርሳቸው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ኢንስፔክተር አለም ገልጸዋል። እርሳቸው በሚመሩት ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር የሚገኙት አቶ አለማየሁ አያቶ መሆናቸውንም አክለዋል።    

ኢዜማ ከሳምንት በፊት መሪው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተገኙበት እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች የተሳተፉበት የምርጫ ቅስቀሳ በባስኬቶ ልዩ ወረዳ አድርጎ ነበር | ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ

ኢዜማ ከሳምንት በፊት መሪው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተገኙበት እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች የተሳተፉበት የምርጫ ቅስቀሳ በባስኬቶ ልዩ ወረዳ አድርጎ ነበር። የልዩ ወረዳው የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባላት እስራት ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተጠየቁት የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ፤ “ኢዜማ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚደረግ ጥረት አካል ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

“በአባላቶቻችን ላይ የሚደርሱ ጫናዎች፣ እስሮች እና ድብደባዎች እኛን ለማሸማቀቅ ያለሙ ናቸው። በእነዚህ ወከባዎች የሚሸማቀቁ አባላት የሉንም” ብለዋል አቶ ዘላለም። 

በባስኬቶ ልዩ ወረዳ በኢዜማ አባላት ላይ እስር ሲፈጸም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ የተናገሩት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ፤ ከዚህ ቀደም በዚያው በደቡብ ክልል በተለይ በኮንሶ ዞን ባሉ የፓርቲው አባላት ላይ “ድብደባ እና ጫና የተለመዱ ክስተቶች ናቸው” ሲሉ ወንጅለዋል። 

ኢዜማ ከመጪው ሀገራዊ ምርጫ ትኩረቱን ላለማንሳት በሚል የአባላቶቹን እስር “እንደማያስጮኸው” የሚናገሩት አቶ ዘላለም፤ ሆኖም በየጊዜው በአባላቱ ላይ የሚደርሱባቸውን ጫናዎች ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሲያሳውቅ መቆየቱን አስረድተዋል። በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የአድአ ወረዳ የምርጫ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ግርማ ሞገስ ባለፈው የካቲት ወር ባልታወቁ ሰዎች ከመገደላቸው በፊት ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየደረሰባቸው ስላለው ወከባ በደብዳቤ ሲገልጹ እንደነበር መነገሩ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)