በኦሮሚያ ክልል በ250 ሚሊዮን ዶላር የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

በቅድስት ሙላቱ

በኢትዮጵያ የወተት እና የወተት ተዋጽኦ ዘርፍ ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋል የተባለ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ በ250 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሊገነባ ነው። በኦሮሚያ ክልል ይገነባል የተባለው ይሄው ፋብሪካ በቀን 250 ሺህ ሊትር ወተት የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሏል። 

ፋብሪካው የሚገነባው ቦሞጅ ስጋ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር በተሰኘ ድርጅት እና መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ባደረገው ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ በተባለ ኩባንያ በጋራ ሽርክና ነው። የቦሞጅ ስጋ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር 93 በመቶ የሚሆነውን የአክሲዮን ድርሻ በባለቤትነት የያዙት በኦሮሚያ ክልል መንግስት ስር የሚተዳደሩ 21 የልማት ድርጅቶች ናቸው። 

ቦሞጅ እና ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ የወተት እና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካውን ግንባታ በተመለከተ ከሁለት ሳምንት በፊት ስምምነት መፈራረማቸውን የቦሞጅ ስጋ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተገኝ ጉደታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ስምምነቱ ሶሶት የስራ ዘርፎችን የሚያካትት እንደሆነም ገልጸዋል። 

በስምምነቱ በቀዳሚነት የተጠቀሰው የወተት ከብቶችን ማርቢያ እና የወተት ምርት ማዕከል (dairy farm) ማቋቋም መሆኑን የሚገልጹት አቶ ተገኝ፤ በሁለተኛነት ስምምነት የተደረሰበት የወተት እና የወተት ተዋጽኦዎችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መሆኑን አስረድተዋል። 

ዋና ስራ አስኪያጁ “10,000 የወተት ከብቶች ይዘን በቀን እስከ 250,000 ሊትር ወተት እናመርታለን ብለን እናስባለን” ሲሉ ፋብሪካው ስራ ሲጀምር የሚኖረውን አቅም ጠቁመዋል።   

በሁለቱ ኩባንያዎች ስምምነት በሶስተኛነት የተቀመጠው የስራ ዘርፍ የመኖ ልማት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ተገኝ፤ በዚህም መሰረት “አልፋ አልፋ” የተሰኘ የእንሳሳት መኖ አይነትን በማምረት ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና ወደ ሰሜን አፍሪካ ሀገራት ለመላክ መታቀዱን አብራርተዋል።  

በእነዚህ የስራ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት የስምምነት ፊርማው የተደረገው በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል ይሁን እንጂ፤ ቦሞጅ ስምምነቱን የፈጸመው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን በመወከልም ጭምር እንደሆነ ዋና ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል። ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ በመጀመሪያ የተገናኘው ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር መሆኑን የሚገልጹት አቶ ተገኝ፤ የኩባንያው ሰዎች ከቦሞጅ ጋር እንዲነጋገሩ የተላኩት በክልሉ መንግስት መሆኑን አስረድተዋል። 

“እኛ ጋር ትልቁ አክሲዮን የመንግስት ስለሆነ፤ ከእኛ ጋር እንዲሰሩ ያመቻቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ነው” ሲሉ  አቶ ተገኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ከተማ ያደረገው ቦሞጅ የስጋ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር 165 ሚሊዮን ብር ይዞ በ21 የአክሲዮን ባለቤቶች የተቋቋመው በ2007 ዓ.ም. ነበር። ከሃያ አንዱ የአክሲዮን ባለቤቶች 93 በመቶ የሚሆነውን የሚይዙት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ናቸው። 

የቦሞጅ ተጣማሪ የሆነው ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ በግብርና እና ምግብ፣ በታዳሽ ሃይል፣ በፍጆታ ዕቃዎች ምርት እና በሪል ስቴት ዘርፎች የተሰማራ እና በግል የኢንቨስትመንት ቡድን ባለቤትነት ስር ያለ ኩባንያ ነው። ከተመሰረተ 60 ዓመታትን የተሻገረው ኩባንያው በአውሮፓ፣ እስያ እና አፍሪካ ባሉ ሀገራት መዋዕለ ንዋዩን ሲያፈስ ቆይቷል። 

ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የገባው በተቀናጀ የግብርና፣ የቁም እንስሳት፣ የወተት ማቀነባበር ልማት ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ እንደሆነ አስታውቋል። ኩባንያው ከቦሞጅ ጋር የመሰረተውን የሽርክና ፕሮጀክት “ኦሮሚያ ግሪን አግሪ ፉድ” በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንደተመዘገበ ተገልጿል።  

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተመዘገበው የሁለቱ ኩባንያዎች የሽርክና ስምምነት መሰረት ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ 51 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን ቦሞጅ የቀሪው 49 በመቶ ድርሻ ባለቤት ይሆናል። ሁለቱ ኩባንያዎች በሌሎች መንግስታዊ ተቋማት የሚፈለጉ ቀጣይ ህጋዊ ሂደቶችን ለማከናወን የሚያስፈልጉ የመተዳደሪያ ስምምነቶችን (memorandum of association and article) በዚህ ሳምንት በተጨማሪነት እንደሚፈራረሙ የቦሞጅ ስጋ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)