የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ስራቸውን ለቀቁ

በሃሚድ አወል

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ቁልፍ የመንግስት ተቋም የሆነውን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ኤባ አባተ ስራቸውን ለቀቁ። ዶ/ር ኤባ ስራቸውን የለቀቁት “በገዛ ፍቃዳቸው” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ከጥር 2009 ጀምሮ ላለፉት አራት አመታት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉት ዶ/ር ኤባ የስራ መልቀቂያቸውን ያስገቡት ከሁለት ወር በፊት ቢሆንም ተቀባይነት ያገኘው ባለፈው ሳምንት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሩ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቃቸው ምክንያት ነው ያሉትን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።  

የዋና ዳይሬክተሩ ከስራ መልቀቅ፤ በተቋማቸው የማስታወቂያ ቦርድ ላይ በተለጠፈ ደብዳቤ በይፋ መገለጹን ሁለት የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የኃላፊው የስራ መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ በደብዳቤው ላይ እንደተጠቀሰም ከሰራተኞቹ አንዱ ተናግሯል።   

ሌላኛው ሰራተኛ በበኩላቸው ደብዳቤው ከተለጠፈበት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዶ/ር ኤባ ምትክ የተተካ ኃላፊ አለመኖሩን ገልጸዋል። ስለጉዳዩ የተጠየቁት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ተስፋዬ፤ ስለ ተተኪው ዋና ዳይሬክተር መረጃ እንደሌላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምላሽ ሰጥተዋል።

ዶ/ር ኤባ ከስራቸው ቢለቅቁም ሌሎች ኃላፊዎች ስራቸው እያከናወኑ እንደሆኑ የሚያስረዱት አቶ ገዛኸኝ፤ “ዋና ዳይሬክተሩ በስራ ገበታቸው ላይ ከሌሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮቹ የሳቸውን ስራ ይሰራሉ” ሲሉ አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአሁኑ ወቅት ሁለት ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አሉት። ከምክትል ዋና ዳይሬክተሮቹ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ ኢንስቲትዩቱ የሚያከናውናቸውን ምርምሮች በበላይነት ይመራሉ። ሌላኛው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ ደግሞ በኢንስቲትዩቱ ስር ያለውን የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከልን በኃላፊነት ያንቀሳቅሳሉ።

ተጠሪነቱ ለጤና ሚኒስቴር የሆነው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአሁኑን ስያሜ ይዞ በአዲስ መልክ የተቋቋመው በጥር 2006 ዓ.ም. ነው። ተቋሙ የተወለደው የኢትዮጵያ ስነ ምግብ ኢንስቲትዩት፣ ብሔራዊ የጤና ምርምር ኢንስቲትዩት እና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር የነበረው የባህል ህክምና ክፍል እንዲዋሃዱ ከተደረገ በኋላ ነው።

ኢንስቲትዩቱ ከሚያከናውናቸው ሶስት ዋና ተግባራት መካከል አንዱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የህክምና ላብራቶሪ ጥራትን ማሻሻል፣ ማዘመን እና ማጠናከር ነው። ሁለተኛው የተቋሙ ኃላፊነት በሀገሪቱ ውስጥ ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት አስፈላጊ ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ ማዘጋጀት እና ከተከሰቱ በኋላም ፈጣን ምላሽ መስጠት ነው። ኢንስቲትዩቱ ከእነዚህ ተግባራት በተጨማሪ የምርምር ስራዎችን የማከናወን ኃላፊነት ተጥሎበታል። 

ተቋሙ በህዝብ ዘንድ ይበልጥ እውቅናን ያገኘው በቀጥታ ከሚመለከተው የወረርሽኝ መከላከል ጉዳይ ነው። የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ከመጋቢት 2012 ጀምሮ ኢንስቲትዩቱ ወረርሽኙን የሚመለከቱ መረጃዎችን በየቀኑ ለህብረተሰቡ ሲያደርስ ቆይቷል። የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል ረገድም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ቁልፍ ሚናዎችን መወጣቱንም ቀጥሏል። 

ኢንስቲትዩቱን እስካለፈው ሳምንት ድረስ በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ኤባ፤ እንደ ጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሁሉ በኮሮና ወረርሽኝ የመከላከል ጥረቶች ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነበሩ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የኢንስቲትዩቱ የስራ ኃላፊ “ዶ/ር ኤባ ሌሊት ገብተው ሌሊት ነው የሚወጡት። ጠንካራ ሰራተኛ ነበሩ” ሲሉ የስራ ትጋታቸውን ይመሰክሩላቸዋል።

ተሰናባቹ ዋና ዳይሬክተር ወደ ኢንስቲትዩቱ ከመምጣታቸው በፊት ለ13 ዓመታት የቆዩት በጎንደር ዩኒቨርስቲ ነበር። ዶ/ር ኤባ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ከቴክኒካል አሲስታንት እስከ ረዳት ፕሮፌሰርነት ባሉ የስራ መደቦች አገልግለዋል። ከጅማ ዩኒቨርስቲ በሜዲካል ላብራቶሪ የትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁት ዶ/ር ኤባ፤ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ከሱዳኑ ካርቱም ዩኒቨርስቲ እና ከስዊድኑ ሊንኮፒንግ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)