ጥቃት የተሰነዘረባቸው የሆሮ ጉድሩ፤ አዲስ አለም አካባቢ ነዋሪዎች “ሙሉ ለሙሉ ተፈናቅለዋል” ተባለ

በሃሚድ አወል

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፤ አቤ ዶንጎሮ ወረዳ ወለጌ ቀበሌ ላይ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች “ሙሉ ለሙሉ” ቀያቸውን ለቅቀው መሰደዳቸውን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ምሽት በተነሰዘረው በዚሁ ጥቃት ሶስት ሰዎች መገደላቸውን ቢያንስ አራት ሰዎች መቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። የዞኑ አስተዳዳሪ የጥቃቱ መፈጸምን እና የሶስት ሰዎችን መገደል ቢያረጋግጡም፤ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ አልተፈናቀሉም ሲሉ አስተባብለዋል።

በወለጌ ቀበሌ “አዲስ አለም” በሚል መጠሪያ ከምትታወቀው አካባቢ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ታጣቂዎቹ በአካባቢያቸው ላይ ተኩስ የከፈቱት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ ጀምሮ ነው። በጥቃቱም ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች ሲገደሉ ስድስቱ ደግሞ መቁሰላቸውን አስረድተዋል። 

በአቤ ዶንጎሮ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የነበሩ የዓይን እማኝ፤ በጥቃቱ የተጎዱ አምስት ሰዎችን በህክምና ቦታው ተመልክቼያለሁ ብለዋል። ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል በስለት የተወጉ እና በጥይት የተመቱ አሉ ያሉት የዓይን እማኙ፤ የተጎጂዎቹ ዕድሜ ከሰባት ወር እስከ ሰማንያ አመት እንደሚሆን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከቁስለኞቹ ውስጥ ሁለቱ ወደ ሻምቦ አጠቃላይ ሆስፒታል “ሪፈር” መባላቸውንም አክለዋል። 

በጥቃቱ ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የሆሮ ጉድሩ ዞን አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ደቻሳ፤ በጥቃቱ የተጎዱት አራት ሰዎች ናቸው ብለዋል። አስተዳዳሪው በተጎጂዎች ቁጥር ላይ ብቻ ሳይሆን “ከአካባቢው ተፈናቅለዋል በተባሉ የነዋሪዎች ብዛት” እና “የጥቃቱ ኢላማ ናቸው” በተባሉ ሰዎች ላይ በነዋሪዎች ከሚነገረው የተለየ መረጃ ሰጥተዋል። 

የአዲስ አለም አካባቢ ነዋሪዎች መኖሪያቸው ጥለው እንዲሸሹ ያደረጋቸው “ማንነት መሰረት ያደረገ ጥቃት” እንደሆነ ቢናገሩም፤ የዞኑ አስተዳዳሪ ገን “ጥቃቱ ማንነትን መሰረት ያደረገ አይደለም” ሲሉ ውንጀላውን ውድቅ አድርገዋል። ጥቃቱን የፈጸሙት “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው” የሚሉት አቶ በቀለ፤ “ሸኔ የአማራም፤ የኦሮሞም ጠላት ነው” ሲሉ ጥቃቱ በሁሉም ላይ የተሰነዘረ መሆኑን ገልጸዋል። 

የዞኑ አስተዳዳሪ “የአካባቢው ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ተፈናቅለዋል” በሚል ከስፍራው የተገኘውን መረጃም አጣጥለዋል። “ውሸት ነው። ህብረተሰቡ  ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ አካባቢውን እየጠበቀ ነው። ይህን የሚያስወሩት በአካባቢው ‘ፋኖ’ በሚል ስም የተደራጁ ጽንፈኞች እና የእነሱ ተላላኪና ጀሌዎች ናቸው” ሲሉ አስተዳዳሪው አስተባብለዋል።   

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አምስት የአዲስ አለም አካባቢ ነዋሪዎች ግን የዞኑን አስተዳዳሪ መረጃ ተቃርነዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአዲስ አለም ነዋሪ “አካባቢዋ አምስት መቶ ሰዎች ይኖሩባት ነበር። አሁን ግን ምንም አይነት ሰው አይገኝም። ሰዎች ወደ አጎራባች አካባቢዎች ሸሽተዋል” ብለዋል። 

ንብረታቸውን ለማውጣት ዛሬ ሐሙስ ወደ አካባቢው የተመለሱ አንድ ነዋሪ በበኩላቸው፤ “አሁን በአካባቢዋ የሚስተዋለው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነው። ምንም ሰው የለም። አካባቢዋ ኦና ሁናለች። መጡባችሁ እያሉን በፍርሃት ውስጥ ነን” ሲሉ በስፍራው ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስረድተዋል። 

“የመንግስት ጥበቃ የለም። ጥቃት ከተፈጸመ እና ጥቃት አድራሾችም ከሄዱ በኋላ ነው የጸጥታ ኃይሎች የሚደርሱት”

– በአቤ ዶንጎሮ ወረዳ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት መኖራቸውን የተናገሩ አንድ ግለሰብ

ከጥቃቱ በተጨማሪ ዝርፊያ መፈጸሙንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት ሶስተኛ የአካባቢው ነዋሪ፤ “ያልተዘረፈ ነገር የለም። የቻሉትን ዘርፈው ያልቻሉትን ደግሞ አቃጥለዋል” ብለዋል። በአካባቢው ዝርፊያ መፈጸሙን ያመኑት የሆሮ ጉድሩ ዞን አስተዳዳሪ፤ “ኦነግ ሸኔ በዞናችን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ስርቆት እና ግድያ እየፈጸመ ነው” ሲሉ ከስሰዋል። 

ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በአቤ ዶንጎሮ ወረዳ መኖራቸውን የተናገሩ አንድ ግለሰብ መንግስት ቸልተኛ ባይሆን ኖሮ ጥቃቱ አይፈጸምም ነበር ሲሉ ወቅሰዋል። “የመንግስት ጥበቃ የለም። ጥቃት ከተፈጸመ እና ጥቃት አድራሾችም ከሄዱ በኋላ ነው የጸጥታ ኃይሎች የሚደርሱት” ሲሉ ተችተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ለህይወታቸው “ዋስትና” የሚሰጣቸው አካል ባለመኖሩም፤ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ስጋት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።  

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የሆሮ ጉድሩ ዞን አስተዳዳሪ፤ “በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ምንም አይነት አስጊ ሁኔታ የለም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”ምላሽ ሰጥተዋል። የጸጥታ እና የፖለቲካ መዋቅሩ ተደራጅቶ አካባቢውን የማረጋጋት ስራ እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ በስፍራው መሰማራታቸውን የሚናገሩት አስተዳዳሪው፤ ከአካባቢው ሚሊሺያዎች ጋር በመቀናጀት ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)