ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 የድምጽ መስጫ ቀን እንዲሆን ወሰነ

● የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ውሳኔም በተመሳሳይ ቀን ይካሄዳል

በተስፋለም ወልደየስ

የመጪው ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሰኞ ሰኔ 14፤ 2013 እንደሚሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። ድምጽ የሚሰጥባቸው ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ያለምንም ችግር በተከናወነባቸው ቦታዎች ብቻ እንደሚሆን የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ዛሬ ሐሙስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ውጭ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 28 እንደሚሆን አስታውቆ ነበር። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ለመመስረት የሚደረገውን ህዝበ ውሳኔ በተመሳሳይ ቀን ለማድረግም ቀን ቆርጦ እንደነበር ይታወሳል።  

የቦርዱ ኃላፊዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረጉት ወቅት፤ የድምጽ መስጫው ቀን ከሁለት እስከ ሶስት ሳምንት ተጨማሪ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ መግለጻቸው የምርጫው መራዘም አይቀሬነትን የጠቆመ ነበር። በዚሁ የውይይት መድረክ ሰኔ 5 እንዲካሄድ ታስቦ የነበረው የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የድምጽ መስጫ ቀን፤ ከሌላው የሀገሪቱ አካባቢ ጋር በተመሳሳይ ቀን እንዲከናወን ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

የምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ አባላት በዛሬው ዕለት ባካሄዱት ስብሰባ አዲሱ የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 14 እንዲሆን ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን የተቋሙ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አስታውቀዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ውሳኔም ከሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫው ጋር ተጣምሮ በዚሁ ቀን እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።   

“የድምጽ መስጫ ቀኑ እንግዲህ ባለፈው ስንናገር ከግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ተነስተን ከሁለት ሳምንት [በኋላ] ነበር ያልነው። ስለዚህ በእኛ በኩል የምንጠብቀው ሰኔ 14 ይሆናል ብለን ነው” ሲሉ ሶልያና ተናግረዋል። 

ሆኖም በመራጮች ምዝገባ ወቅት አቤቱታ የቀረበባቸው፣ በጸጥታ ችግርም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው እንዲሁም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ባሉ ቦታዎች ግን በሰኔ 14 ድምጽ እንደማይሰጥ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊዋ አመልክተዋል። በእነዚህ ምክንያቶች በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሐረሪ እና በአማራ ክልሎች ባሉ የተወሰኑ ቦታዎች የድምጽ መስጠት ሂደቱ በዕለቱ እንደማይከናወን ጠቁመዋል።  

በሶማሌ ክልል የድምጽ አሰጣጡ በተባለው ቀን የማይካሄድባቸው ሰባት የምርጫ ክልሎች እንደሆኑ የገለጹት ሶልያና፤ የዚህ ምክንያቱም በእነዚህ ቦታዎች በመራጮች ምዝገባ ወቅት ችግሮች ተስተውለዋል በሚል ለቦርዱ አቤቱታ በመቅረቡ እንደሆነ አስታውሰዋል። ቦርዱ በእነዚህ የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ እንዲቆም በማድረግ ማጣራት መጀመሩንም ገልጸዋል። የማጣራት ስራውን የሚያከናውኑ 10 ቡድኖች የተወሰኑቱ ወደ ስፍራዎቹ መሄዳቸውንም  አስረድተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስር ባለው የመተከል ዞን፤ የመራጮች ምዝገባ እስካሁን አለመጀመሩን የሚናገሩት የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ፤ ከአካባቢው በርካቶች መፈናቀላቸው ጋር ተዳምሮ በዞኑ በሰኔ 14 ድምጽ እንደማይሰጥ አስታውቀዋል። በእነዚህ ቦታዎች የሚደረገው የድምጽ አሰጣጥ “አሁን ካለው ሰኔ 14 ውጭ የሚታይ ነው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)