በቅድስት ሙላቱ
የእነ አቶ ስብሃት ነጋ ጠበቆች በቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደት ላይ ያቀረቡት አቤቱታ፤ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርብ ወይም አያስቀርብ እንደሆነ ለመወሰን ለሰኞ ግንቦት 16 ቀጠሮ ተሰጠ። ቀጠሮውን የሰጠው ዛሬ አርብ ግንቦት 13 የተሰየመው አንደኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ነው።
የተጠርጣሪ ጠበቆች አቤቱታውን ለሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት፤ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደትን በተመለከተ የፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰኗቸውን ውሳኔዎች በመቃወም ነው። አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ 42 ተጠርጣሪዎችን የወከሉት ጠበቆች አቤቱታቸውን በጹሁፍ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያስገቡት ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ግንቦት 11 ነበር።
ከጠበቆቹ መካከል ሶስቱ፤ ጉዳዩን ለማድመጥ ዛሬ ለተሰየመው ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን በዝርዝር አስረድተዋል። ጠበቆቹ በማብራሪያቸው በስር ፍርድ ቤቶች የተላለፉት ውሳኔዎች “መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለባቸው” ብለዋል። ውሳኔዎቹ ስምንት የህግ ስህተቶች እንዳሉባቸው የጠቆሙት ጠበቆቹ፤ እነዚሁኑ በአጭሩ ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።
በአቤቱታው ከተነሱ መሰረታዊ የህግ ስህተቶች መካከል፤ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔዎች “ለምስክሮች ጥበቃ ሲደረግ ሊሟሉ የሚገባቸውን መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች እና ስነ ስርዓታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የተሰጠ ነው” የሚለው በዋነኛነት ተጠቅሷል። ጠበቆቹ ይህንንም ሲያስረዱ “ፍርድ ቤቱ የተረጋገጠ ነገር ሳይኖር ግምት በመውሰድ ብቻ የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት አለበት” ብለዋል። ለምስክሮች ጥበቃ ማድረግ የሚቻለው ምስክሩ የሚያስረዳው ነገር በሌላ በማንኛውም ሁኔታ መረጋገጥ የማይችል ከሆነ እንደው ያስታወሱት ጠበቆቹ፤ የስር ፍርድ ቤት ግን “ይህን ሳያመዛዝን ግምት በመውሰድ ብቻ ውሳኔ አስተላልፏል” ብለዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በተመለከተበት ወቅት፤ ዐቃቤ ህግ ለምስክሮች ደህንነት ሲል ጥበቃ በማድረጉ ምክንያት የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደቱ በዝግ ችሎት እንዲሆን መጠየቁን ጠበቆቹ በአቤቱታቸው አንስተዋል። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መልሶ ክርክር እንዲደረግበት ከታዘዘ በኋላ ግን ዐቃቤ ህግ ቀደም ሲል በክርክሩ ላይ የጠቀሰውን ምክንያት “ለሀገር ደህንነት ሲባል ነው” በሚል መቀየሩን ጠቅሰዋል። የታችኛው ፍርድ ቤትም ይሄንኑ መነሻ በመድረግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እንዲሆን መወሰኑ ተገቢ አይደለም ሲሉም አክለዋል።
በተጨማሪም ዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እንዲሆን የፈለገው “ሚዲያዎች አዛብተው እንዳይዘግቡ” በሚል እንደሆነ ጠበቆች አስታውሰዋል። ነገር ግን ሚዲያ እንዳይዘግብ ማድረግ እና ዝግ ችሎት ይሁን ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው ያሉት ጠበቆቹ፤ ሚዲያ እንዳይዘግብ ከተፈለገ ዝግ ችሎት ሳይሆን በሌላ መንገድ መከልከል ይቻላል ብለዋል። ሚዲያዎችን እንዳይዘግቡ ሲባል ብቻ ችሎቱ በዝግ መሆን የለበትም ሲሉ የተከራከሩት ጠበቆች “መረጃ ከኛ ጠይቀው ሊዘግቡ ይችላሉ ” ብለዋል።
የጠበቆቹን ማብራሪያ ያደመጠው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንደኛ ሰበር ሰሚ ችሎት፤ ጉዳዩ ለምርመራ ያስቀርብ ወይም አያስቀርብ እንደሆነ ለመወሰን ለሰኞ ግንቦት 16 ቀጠሮ ሰጥቷል። ችሎቱ በዚሁ ዕለት በተጠርጣሪ ጠበቆች የቀረበ የእግድ ጥያቄን እንደሚመለከትም አስታውቋል። የእግድ አቤቱታው፤ የፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን በዝግ ችሎት ለመስማት የያዘው ቀጠሮ በተያዘለት ቀን እንዳይካሄድ የሚጠይቅ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)