በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመሰማራት በተደረገው ዓለም አቀፍ ጨረታ የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የብሪታኒያው ቮዳፎን እና የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮም የተካተቱበት ጥምረት አሸነፈ። ጥምረቱ ያሸነፈው ከፍተኛ የፈቃድ ክፍያ ዋጋ እና አስተማማኝ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዕቅድ በማቅረቡ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታውቀዋል።
ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 14 አሸናፊነቱ ይፋ የተደረገው “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” የተሰኘው ጥምረት፤ የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እና የብሪታኒያው የልማት ፋይናንስ ተቋም ሲዲሲ ግሩፕን ጨምሮ አምስት ኩባንያዎች እና ተቋማት የተቀናጁበት ነው። ጥምረቱ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድን ለማግኘት የመወዳደሪያ ሰነዶቹን ያስገባው ሚያዝያ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር።
እነ ሳፋሪኮም ከፈጠሩት ጥምረት ጋር ለመፎካከር በብቸኝነት የቀረበው ሌላው ተወዳዳሪ የደቡብ አፍሪካው ኤም.ቴ. ኤን ነው። የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ሁለቱም ተጫራቾች “የጨረታውን መስፈርት የሚያሟሉ ሆነው ተገኝተዋል።”
ሆኖም ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” የተሰኘው ጥምረት የኦፕሬሽን ፈቃድ ለማግኘት ባቀረበው የገንዘብ መጠን እና በመዋዕለ ንዋይ ፍሰቱ ተመራጭ ሊሆን መቻሉ ተገልጿል። በአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) የሚደገፈው የእነ ሳፋሪኮም ጥምረት፤ አንድ የኦፕሬሽን ፈቃድ ለማግኘት 850 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ አቅርቧል። ከቻይናው ሲልክ ሮድ ፈንድ ጋር በመጣመር በጨረታው የተወዳደረው ኤም.ቲ. ኤን ያቀረበው ዋጋ ከእነ ሳፋሪኮም ጥምረት በ250 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ ነው።
“ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” የተሰኘው ጥምረት በአጠቃላይ ከስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ መዋዕለ ንዋይ በኢትዮጵያ የማፍሰስ እቅዱን በጨረታው ሰነድ ማካተቱ ተገልጿል። የጥምረቱን እቅድ “አስተማማኝ” ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ የቀረበው የገንዘብ መጠን “እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ከተደረጉት የውጪ ቀጥተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች ብልጫ እንዲኖረው ያደርገዋል” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
በቮዳፎን የሚመራው ጥምረቱ ይህን ጨረታ አሸንፎ የኦፕሬሽን ፈቃዱን በእጁ ካስገባ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንደሚፈቀድለት ቀደም ሲል ተገልጾ ነበር። ብድሩ “ለንድፍ ግንባታ እና ስራ ማስኬጃ” የሚውል እንደሆነም ተመልክቷል። ጥምረቱ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ሲሰማራ ለ1.5 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” ለተሰኘው ጥምረት አዲስ ሀገር አቀፍ የቴሌኮም ፍቃድ እንዲሰጠው የወሰነው ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 14 ባደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ነው። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ለጥምረቱ ፍቃድ እንዲሰጥ የወሰነው “በአንድ ድምጽ” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ገልጸዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ስብሰባ ያጸደቀው ለአንድ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ፍቃድ እንዲሰጥ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በኩል ባለፈው ህዳር ያወጣው ጨረታ ግን ለሁለት የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃዶች ነበር። ምክር ቤቱ “ሁለተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ” ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዛሬ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)