በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሐይማኖት የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን መመዝገብ ሊጀምር ነው። ከአስር ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚጀመረው ምዝገባ ለአንድ ወር ያህል ይቆያል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አቶ መሐመድ ኢድሪስ ምዝገባው ያስፈለገበት ምክንያት በመጋቢት 2013 በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ስራ ላይ የዋለው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፤ የሐይማኖት ተቋማት የብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ እንዲያገኙ በመደንገጉ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡
ከሁለት ወራት በፊት የጸደቀው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ “የሐይማኖት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ እንደማይሰጣቸው” የሚደነግገውን የቀድሞውን የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ በመሻር ተቋማቱ በብሮድካስት አገልግሎት እንዲሳተፉ ፈቅዷል። የሐይማኖት ቴሌቪዝን ጣቢያዎቹ ከአስር ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይፋ በሚደረገው የምዝገባ ጥሪ መሰረት ለመመዝገብ ሲመጡ ሶስት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አቶ መሐመድ ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ፤የቴሌቪዥን ጣቢያው አስተምህሮቱን የሚያስተላልፍለት የሐይማኖት ተቋም በሰላም ሚኒስቴር የተመዘገበ መሆን ነው። ሁለተኛው የሐይማኖት ተቋሙ ለጣቢያው የሚሰጠው የድጋፍ ደብዳቤ ሲሆን፤ የመጨረሻው መስፈርት ደግሞ እንደማንኛውም የንግድ ድርጅት ከሚመለከተው የመንግስት አካል የሚሰጥ ዕውቅና ነው።
በአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የተሰጣቸውን መብት ተጠቅመው የሚመዘገቡ የቴሌቪዝን ጣቢያዎች “ተገቢውን ጥበቃ እና እገዛ ያገኛሉ” ሲሉ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “በተሰጠው ቀነ ገደብ የማይመዘገቡ ጣቢያዎችን እንደ ህገ ወጥ ነው የምናያቸው” የሚሉት አቶ መሐመድ፤ “ህገ ወጥ ተቋማቱን ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንሰራለን” ሲሉ በቁጥጥሩ ላይ ዐቃቤ ህግ እና ፖሊስ ጭምር እንደሚሳተፉበት አስታውቀዋል።
ሐይማኖታዊ ይዘቶችን ብቻ የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን በብሮድካስት አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ በአዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቢፈቀድም፤ አሁንም ቢሆን ግን እነዚህን መሰል ተቋማት የሬድዮ የስርጭት ሞገድ ማግኘት ላይ ገደብ ተጥሎባቸዋል። በአዋጁ አንቀጽ 40 ላይ የሐይማኖት ተቋማት “ውስን በሆነ የሬዲዮ ሞገድ በመጠቀም የብሮድካስት አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ አይሰጣቸውም” የሚል ድንጋጌ ሰፍሯል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “ለኢትዮጵያ በአለም የቴሌኮሙኒኬሽን ማህበር ለብሮድካስት አገልግሎት የተመደበው የራዲዮ ሞገድ ውስን በመሆኑ ይህን ውስን ሃብት ላለማባከን ነው” በማለት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ ማለት ግን ውስን የሆነውን የሬዲዮ ሞገድ የማይጠቀሙ እንደ ሳተላይት ሬድዮ አይነቶቹ የብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ አይነቶች ሊሰጣቸው እንደሚችል በአዋጁ ጭምር መደንገጉን ገልጸዋል።
ከሐይማኖት የመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ ለበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ዕውቅና የሰጠው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው በጥር 2013 መጨረሻ ነው። የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ፤ ቀደም ሲል የመገናኛ ብዙኃንን ምዝገባ እና ፍቃድ ሲያስፈጽም የነበረው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ስያሜውን ወደ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ቀይሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)