አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ገደብ ጣለች

ለትግራይ ቀውስ ተጠያቂ የተባሉ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ባለስልጣናት፣ የአማራ ክልል ኃይል እና የህወሓት አባላት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል የቪዛ ገደብ ተጣለባቸው። በባለስልጣናት ላይ ከተጣለው የቪዛ ክልከላ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ መንግሥት በሚሰጥ የኢኮኖሚ እና የጸጥታ ዕርዳታ ላይ ገደብ መጣሉን የአሜሪካ መንግስት አስታውቋል። 

የቪዛ ክልከላውን እና ገደቡን ትናንት እሁድ ግንቦት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ያደረጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ናቸው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት የመንግስታቸው እርምጃ የሚመለከተው በትግራይ ለተፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ እና ተባባሪ የሆኑ እንዲሁም ቀውሱን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ያስተጓጎሉ የተባሉትን ነው።

በመግለጫው ላይ በስም ባይዘረዘሩም የቀድሞ እና አሁን በስራ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ባለስልጣናት እና የጸጥታ አስከባሪ ተቋማት አባላት የቪዛ ክልከላ ተጥሎባቸዋል። ክልከላው የአማራ ክልል ኃይል፣ መደበኛ ያልሆኑ ኃይሎች እና የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አባላትን ይጨምራል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ወታደሮች በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ስርጭትን ይከለክላሉ የሚል ብርቱ ትችት ባለፈው ሳምንት ከሰነዘሩ በኋላ የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ክፉኛ ላሽቋል። አሁን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ ለተጣለው የጉዞ ገደብ አንዱ መነሾም ይኸው የሰብዓዊ ዕርዳታ ስርጭት የገጠመው ዕክል ነው። 

ማዕቀቡ በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ የተለያዩ በደሎች የፈጸሙ እና በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደርስ ያስተጓጎሉትን የሚያካትት እንደሆነ በመግለጫው ተጠቁሟል። ማዕቀቡ “እንዲህ አይነት ድርጊት የፈጸሙ ግለሰቦች የቅርብ ቤተሰቦችም ገደቡ ሊመለከታቸው ይችላል” ሲል መግለጫው አትቷል። 

“በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ በሚሰጥ ኢኮኖሚያዊ እና የጸጥታ ድጋፎች ላይ ዘርፈ ብዙ ገደቦች ጥለናል” ያሉት አንቶኒ ብሊንከን፤ “የመከላከያ ንግድ ቁጥጥር ፖሊሲም ከዚህ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ይደረጋል” ብለዋል። በመግለጫው መሠረት በኤርትራ ላይ ተጥለው የቆዩ ሰፊ የዕርዳታ ገደቦች ባሉበት ይቀጥላሉ። 

ይሁንና የሰብዓዊ ዕርዳታን ጨምሮ ጤና፣ የምግብ ዋስትና፣ መሠረታዊ ትምህርት፣ ለሴቶች እና ልጃገረዶች የሚሰጥ ድጋፍ፣ የሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሁም ግጭት አፈታትን በመሳሰሉ ዘርፎች አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምትቀጥል አስታውቃለች። 

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫቸው በትግራይ የሚኖሩ ሕዝቦች በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ስቅየት፣ የጭካኔ ድርጊቶች አሁንም እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጸው “እጅግ አንገብጋቢ የሆነው የሰብዓዊ ዕርዳታ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ጦሮች እንዲሁም በሌሎች ታጣቂዎች እየተስተጓጎለ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል። 

ብሊንከን በክልሉ ይፈጸማሉ ያሏቸውን ግድያ፣ በኃይል ማፈናቀል፣ ወሲባዊ ጥቃት እና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አሜሪካ እንደምታወግዝ ገልጸዋል። የውሃ ምንጮች፣ ሆስፒታሎች እና የሕክምና ተቋማትን ጨምሮ በህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ደርሰዋል ያሏቸውን ውድመቶች ኮንነዋል። 

“ግጭቱ በአፋጣኝ ቆሞ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ካልተስፋፋ ወቅታዊው እና የከፋው የምግብ እጥረት ወደ ጠኔ ሊመራ ይችላል” ሲሉ ብሊንከን ስጋታቸውን ገልጸዋል። ስድስት ወራት ገደማ ባስቆጠረው የትግራይ ግጭት ከሚሳተፉ ወገኖች ጋር ተደጋጋሚ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ቢደረጉም፤ “ፖለቲካዊውን ቀውስ በሰላም ለመፍታት ትርጉም ያለው እርምጃ አልወሰዱም” ሲሉም በጉዳዩ እጃቸው አለበት የተባሉ ኃይሎች መፍትሄ አለማምጣታቸውን አንስተዋል።    

በትግራይ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስታት እርምጃዎች እንዲወስዱ ጥሪ ያቀረቡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ሀገራቸው ተጨማሪ እርምጃዎች እንደምትወስድ አስጠንቅቀዋል። ብሊንከን ለኢትዮጵያ መንግስት ያቀረቡት ጥሪ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚጠየቁትን ለህግ እንዲያቀርብ፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቅ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ያለ ገደብ እንዲፈቅድ ነው።

እስካሁንም በትግራይ ክልል ይንቀሳቀሳሉ ስለሚባሉት የኤርትራ ወታደሮችን በተመለከተ ደግሞ “የኤርትራ መንግሥት በአደባባይ የገባውን ቃል እንዲያከብር እና ወታደሮቹን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ወደተሰጠው የኤርትራ ድንበር እንዲመልስ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል። “በትግራይ የተፈጠረው ቀውስ እንዳይፈታ እንቅፋት የሚፈጥሩ አካሔዳቸውን ካልቀየሩ ከአሜሪካ እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጨማሪ እርምጃ ይጠብቁ” የሚል ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያም አያያዝው ሰንዝረዋል። 

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌሎች መንግስታትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል። ብሊንከን ባለፈው ሳምንት ከፊንላንድ አቻቸው እና የአውሮፓ ህብረት መልዕክተኛ ፔካ ሀቪስቶ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ሁኔታ እና የትግራይ ቀውስ ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)