በአሜሪካ እርምጃ ማዘኑን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት፤ ለቀረቡበት ክሶች መልስ ሰጠ

10

አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ክልከላ በማድረግ “ተገቢ ያልሆነ ጫና ማሳደር መቀጠሏ” እንዳሳዘነው የኢትዮጵያ መንግስት ገለጸ። ኢትዮጵያ በመጪው ሰኔ አጋማሽ ብሔራዊ ምርጫ ለማካሔድ በዝግጅት ላይ በምትገኝበት ወቅት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትላንት ይፋ ያደረጉት እርምጃ “የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል” ብሏል። 

ከወደ ዋሽንግተን ከተሰማው ጠንከር ያለ እርምጃ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት አቋሙን ያሳወቀው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በኩል ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የአሜሪካ መንግስት የወሰደውን እርምጃ ከመኮነን ባሻገር በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ዘርዝሯል።

የሚኒስቴሩ መግለጫ “አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመግባት የምታደርገው ጥረት ተገቢ ያልሆነ እና በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው” በሚል እርምጃውን ተቃውሟል። ሚኒስቴሩ እንዳለው “ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮቿን እንዴት ማካሄድ እና ማስተዳደር እንዳለባት ሊነገራት አይገባም።”

በአፍሪካ ቀንድ የረዥም ዘመናት የአሜሪካ የቅርብ አጋር ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ፤ ከትግራይ ውጊያ በኋላ ከዋሽንግተን ያላት ግንኙነት ቀስ በቀስ እየሻከረ ሔዶ እጅግ ዝቅተኛ የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዩ መልዕክተኛ ሴናተር ክሪስ ኩንስ እና የአገሪቱ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ውይይቶች ቢያደርጉም፤ የአሜሪካ መንግስት በሚያወጣቸው መግለጫዎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀስ በቀስ እየበረታ ሲሔድ ታይቷል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትን የጉዞ ቪዛ የሚከለክለው ውሳኔ የተላለፈው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ እና ገንቢ ግንኙነት በጀመረበት ወቅት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ጠቅሷል። መንግስት የአሜሪካ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክን የተቀበለው በዚሁ አዎንታዊ ስሜት እንደነበርም አስታውሷል። 

ሆኖም የአሜሪካ መንግስትን ውሳኔ “የተሳሳተ እርምጃ” ሲል የጠራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፤ ውሳኔው “አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ያመጣል” በሚል ተስፋ በተደረገበት በመጪው ምርጫ የሚያጠላ መሆኑን አስታውቋል። ሰኔ 14 ቀን 2013 የሚካሄደው ምርጫ “ለአካታች ውይይት መንገድ ይጠርግ ነበር” ያለው መግለጫው፤ ሆኖም ሀገሪቱ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በምትዘጋጅበት ወቅት አሜሪካ ይህን አይነት ውሳኔ ማስተላለፏ “የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል” ሲል ነቅፏል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ በትግራይ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ረገድም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተከናውኗል ያላቸውን የእርምት እርምጃዎች ዘርዝሯል። የኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊነት ያለባቸውን ተጠያቂ በማድረግ ቃሉን እያከበረ እንደሚገኝ የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ ለዚህም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በትግራይ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያደረገውን ምርመራ አጠናቆ ይፋ ማድረጉን በማሳያነት ጠቅሷል።

ሌላው በመግለጫው የተነሳው ክንውን፤ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የጋራ ምርመራ መጀመራቸው ነው። የአፍሪካ የሰብዓዊ እና የሰዎች መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ መንግስት ግብዣ ምርመራዎች እያከናወነ መሆኑም በተጨማሪ ማሳያነት ተነስቷል። 

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እና የግብረሰናይ ድርጅቶች ገጥሟቸዋል ያሉት ተግዳሮት፤ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ላይ ለወሰደችው እርምጃ አንዱ ገፊ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው ነበር። ሚኒስትሩ ትናንት እሁድ ባወጡት መግለጫ “እጅግ አንገብጋቢ የሆነው የሰብዓዊ ዕርዳታ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ጦሮች እንዲሁም በሌሎች ታጣቂዎች እየተስተጓጎለ ነው” በማለት ወንጅለዋል። 

ይህን የብሊንከንን ክስ ውድቅ ያደረገው የዛሬው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፤ በሁሉም የትግራይ ክልል አካባቢዎች ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ሙሉ እና ያልተገደበ እንቅስቃሴ መፈቀዱን ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት “ያለውን አነስተኛ ሀብት እና አጋሮቹን በማሰባሰብ አስቸኳይ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ለመድረስ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ችግሩ የአቅም እና ተጨማሪ ሀብት እጦት እንጂ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዳልሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ” ሲልም ምላሽ ሰጥቷል። 

የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካንን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ካደረጋቸው ተከታታይ ውይይቶች በኋላ የተወሰኑ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጾ፤ የአሜሪካ መንግስት እርምጃ ግን ገንቢ ያለውን ግንኙነት እና የተገኙ ስኬቶችን ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ጭምር ይጎዳል ብሏል። 

“የአሜሪካ አስተዳደር፤ የኢትዮጵያን መንግስት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀው ህወሓት እኩል አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ ማሳየቱ” በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “ይበልዝ አሳዛኝ” ተብሎ ተጠቅሷል። መንግስት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ውይይትን ለማጠናከር ያለማቋረጥ እየሰራ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ ሆኖም ከህወሓት ጋር የሚደረግ ድርድር እንደማይኖር በአጽንኦት አመልክቷል። “ሽብርተኛውን ህወሓት መልሶ ለማንሰራራት የሚደረግ ማናቸውም ጥረት የማይሳካ እና የማይቻል ነው” ሲልም ጠንከር ያለ አቋሙን አሳውቋል። 

“በውስጣዊ ጉዳያችን ጣልቃ የመግባት እና መቶ አመታት ገደማ የዘለቀ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን የሚያዳክም እንዲህ አይነት እርምጃ ካልተገታ የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደገና ለመገምገም ይገደዳል። ይኸ ደግሞ ከሁለትዮሽ ግንኙነታችን ባሻገር ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል” ሲል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)