እነ ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ በመጪው ጥር አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አስታወቁ

አምስት ኩባንያዎች እና ተቋማትን ያካተተው “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” የተሰኘው ጥምረት የሚያቋቁመው ኩባንያ፤ በኢትዮጵያ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የማቅረብ ስራውን ከሰባት ወራት ገደማ በኋላ በጥር 2014 ዓ.ም. ለመጀመር እንዳቀደ አስታወቀ። አዲሱ ኩባንያ አሁን በሀገሪቱ በብቸኝነት የቴሌኮም አገልግሎት እየሰጠ ያለውን ኢትዮ ቴሌኮምን የሚገዳደር ነው ተብሎለታል። 

በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት ይህን ያስታወቀው ትላንት ሰኞ ግንቦት 16 ባወጣው መግለጫ ነው። ጥምረቱ የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ ለመስጠት ያወጣውን ጨረታ ማሸነፉ በይፋ ከተገለጸ በኋላ መግለጫ ሲያወጣ የትላንቱ የመጀመሪያው ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ለሁለት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ያወጣው ባለፈው ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ከተካተቱ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አበይት እቅዶች አንዱ በሆነው እና የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ ለውድድር የሚከፍተው የጨረታ ዝግጅት ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ጭምር የተሳተፈበት ነው። 

በጨረታው ለመሳተፍ 12 ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን የጨረታ ሰነድ ያስገቡት የእነ ሳፋሪኮም ጥምረትን ጨምሮ ሁለት ተወዳዳሪዎች ብቻ ናቸው። “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” በተሰኘው ጥምረት ውስጥ አምስት ኩባንያዎች እና ተቋማት የተካተቱ ሲሆን መቀመጫውን በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ያደረገው እና 35 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሳፋሪኮም ጥምረቱን ይመራል።

የሳፋሪኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር ንዴግዋ፤ “የዲጂታል የአኗኗር ዘይቤ ለማቅረብ የቴሌኮም ኔትወርክ በመዘርጋት ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር የመስራት ዕድል በማግኘታችን ደስተኞች ነን። በኢትዮጵያ ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር በመስራት ተመሳሳይ ለውጥ ማቅረብ በዚያውም ለባለድርሻዎቻችን ዘላቂ ትርፍ ማስገኘት እንችላለን” ሲሉ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ተስፋ እንደጣሉ የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል።   

እንደ ሳፋሪኮም ሁሉ የጥምረቱ አባል የሆኑት የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮም እና የብሪታንያው ቮዳፎን፤ የቴሌኮም አግልግሎት በማቅረብ የሚታወቁ ግዙፍ ኩባንያዎች ናቸው። የቮዳኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻሜል ጆሱብ “የጥምረቱ አባላት፤ ጥራት ባለው የቴሌኮም ኔትወርክ የተገነባ ለውጥ የሚያመጣ የቴክኖሎጂ አገልግሎት በተለይም በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና ዘርፎች በማቅረብ የተመሰከረላቸው ናቸው” በማለት አምስቱ ኩባንያዎች እና ተቋማት የዲጂታል አገልግሎትን በማስፋፋት በኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ “ተጨባጭ ለውጥ” የማምጣት ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል። 

የብሪታኒያው ቮዳፎን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኒክ ሬድ በበኩላቸው “ይኽ የቴሌኮም ውድድርን መፍቀድ ከመጨረሻዎቹ ግዙፍ የዓለም ገበያዎች አንዷ ለሆነችው ለኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ለውጥ ነው። የሚቀጥለው ትውልድ የቴሌኮም እና የዲጂታል አገልግሎትን ስራ ላይ በማዋል የኢትዮጵያ ግዙፍ የኢኮኖሚ እና የልማት አቅም መሳካቱን ለማረጋገጥ እና አካታች እና ዘላቂ የዲጂታል ማህበረሰብ ለመፍጠር ቁልፍ ሚና መጫወት እንፈልጋለን” ብለዋል። 

በ“ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” ባለድርሻ የሆኑት የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እና የብሪታንያው የልማት ፋይናንስ ተቋም (CDC Group) ኃላፊዎች ኢትዮ ቴሌኮምን ይገዳደራል ተብሎ የሚጠበቀው ኩባንያ ለኢትዮጵያውያን ደንበኞቹ ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት የተቆራኘ ፋይዳ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል። የሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋና የዲጂታል ኦፊሰር ቶሺካዙ ናምቡ ኩባንያው በእስያ እና በጃፓን ያካበተውን የዳበረ ልምድ እና እውቀት ወደ ኢትዮጵያ የመውሰድ ዕቅድ እንዳለው ጠቁመዋል። 

የብሪታንያው የልማት ፋይናንስ ተቋም የአፍሪካ ቢሮ ኃላፊ ትንቢተ ኤርሚያስ በበኩላቸው “ከከተማ ነዋሪዎች እስከ ገበሬዎች፤ ለትላልቅ እና አነስተኛ ነጋዴዎች  በአስር ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች የሚያቀርብ ዘመናዊ ኔትወርክ ለመዘርጋት ዝግጁ ነን” ብለዋል። “ዘመናዊ፣ የተረጋጉ እና አዳጊ ኢኮኖሚዎች የተገነቡት በአስተማማኝ እና በተመጣጣኝ ዋጋ በሚቀርብ የዲጂታል መሰረተ ልማት፣ ለዓለም አቀፍ ንግድ ባለ ዕድል ላይ ነው” ሲሉም አገልግሎቱ የሚያመጣውን ትሩፋት አስረድተዋል። 

የጥምረቱ አባላት፤ ከ112 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አሉት በሚሉት የኢትዮጵያ ገበያ ሲሰማሩ ሊያበረክቱት ስለሚችሉት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ገፋ ሲልም ስለሚያገኙት ትርፍ ትናንት ሰኞ ባወጡት መግለጫ ቢናገሩም፤ በአበዳሪያቸው አሜሪካ እና በገበያቸው ኢትዮጵያ መካከል የበረታው መጎማዘዝ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ሳይጠቅሱ አልፈዋል። 

የአሜሪካ የልማት ባንክ የሆነው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) ጥምረቱ ጨረታውን ካሸነፈ “ለንድፍ፣ ግንባታ እና ስራ ማስኬጃ” 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ተስማማቶ ነበር። ሆኖም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ ሀገራቸው ከትናንት በስቲያ እሁድ በኢትዮጵያ በባለስልጣናት ላይ ከጣለችው የቪዛ ክልከላ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ መንግስት በምትሰጠው የኢኮኖሚ እና የጸጥታ ዕርዳታ ላይ ገደብ መጣሉን ማስታወቃቸው የብድሩ ሂደት ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር ተሰግቶ ነበር። 

“ብሎምበርግ” የተሰኘው አለም አቀፍ የዜና አገልግሎት ትላንት ማምሻውን ባወጣው ዘገባ፤ በዚህ ማዕቀብ ሳቢያ የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ለጥመርቱ ሊሰጠው ቃል የገባው ብድር ጥያቄ ውስጥ እንደወደቀ ዘግቧል። በትግራይ ቀውስ ሳቢያ በኢትዮጵያ ላይ ጠንከር ያለ ጫና ማሳደር የመረጠችው አሜሪካ ብድሩን ከከለከለች፤ የጥምረቱ አባላት አዲስ የገንዘብ ምንጭ ማፈላለግ ይኖርባቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)