እነ ጃዋር መሐመድ ከዛሬ ጀምሮ ፍርድ ቤት መቅረብ አንፈልግም አሉ

በቅድስት ሙላቱ

በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ 24 ተከሳሾች ከዛሬ ጀምሮ ጉዳያቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ አስታወቁ። ተከሳሾቹ በትግራይ እየተካሄደ ነው ያሉትን “የጅምላ ግድያ እና ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ” ለመቃወም ለሁለት ቀናት የረሃብ አድማ እንደማዲያደርጉም ገልጸዋል።  

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ያለመቅረብ ውሳኔያቸውን ያስታወቁት፤ መደበኛ የክስ ሂደታቸውን እየተመለከተ ላለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ-ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 18 በጽሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ ነው። በችሎቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ጃዋር መሐመድ፤ የኮሎኔል ገመቹ አያና እና የሌሎች ተከሳሶችን ጉዳይ በመጥቀስ የፍርድ ቤት ውሳኔ በተገቢው መንገድ ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም ብለዋል። 

“እኛ እዚህ የመጣነው ከተፈረደብን ለመቀጣት፤ ነጻ ከተባልን ለመውጣት ነው” ያሉት አቶ ጃዋር፤ “ከዛሬ ጀምሮ በገዛ ፍቃዳችን ፍርድ ቤት አንቀርብም” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል። ይህንን ውሳኔ ደግፈው የተናገሩት አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው “በግድ ተጎትተን እና ተደብድበን ካልሆነ በቀር ወደዚህ ፍርድ ቤት አንመጣም” ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ጃዋር ወደ ፍርድ ቤት ላለመምጣት መወሰናቸውን ከማስታወቃቸው በተጨማሪም በትግራይ ክልል እየተከሰተ ላለው ሁኔታ የትግራይ ህዝብ የረሃብ አድማ ላይ በመሆኑ፤ እነርሱም ለሁለት ቀናት ምግብ እንደማይበሉ ተናግረዋል። የረሃብ አድማው በትግራይ ክልል በትግራይ ክልል እየታየ ያለውን “የጅምላ ግድያና ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ ለመቃወም” መሆኑን ተከሳሹ አስረድተዋል።

በዛሬው ችሎት መጀመሪያ ላይም በአካል ፍርድ ቤት የተገኙ 21 ተከሳሾች በትግራይ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በደምቢዶሎ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የህሊና ጸሎት አድርገዋል። ከፍርድ ቤት ፍቃድ ውጪ የተደረገው ይህ የህሊና ጸሎት ለአንድ ደቂቃ የሚቆይ ነው የተባለ ቢሆንም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቋል። 

አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለ ለችሎቱ ያሰሙትን ንግግር ተከትሎ፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሌላኛው አመራር የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ፍርድ ቤቱ ሳይፈቅድላቸው የተናገሩት አቶ ደጀኔ “የኦሮሞ ህዝብ ለዚህች ሀገር ጠላት ሆኖ ተፈርጇል” ሲሉ ወንጅለዋል። በማስከተልም “የኦሮሞ ህዝብ አንድ ሆናችሁ ይህንን መንግስት እንታገል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል። 

ፍርድ ቤቱም በበኩሉ ተከሳሾቹ ያነሱት ሀሳብ ላይ ምክር ሰጥቷል። “የእኛ እምነት ነጻ ከሆናችሁ እናንተን ነጻ ማውጣት ነው” ያለው ፍርድ ቤቱ፤ ይሄንንም በሂደት ለተከሳሾቹ እንደሚያረጋግጥላቸው ቃል ገብቷል። ፍርድ ቤቱ የዛሬውን ችሎት ከማጠናቀቁ በፊት ለመደበኛ የክስ ሂደቱ ሁለት ቀጠሮዎችን ሰጥቷል። 

የመጀመሪያው ቀጠሮ ዐቃቤ ህግ በእነ ጃዋር መሐመድ ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች ላይ አሉ የሚላቸውን የደህንነት ስጋቶች ዘርዝሮ በግንቦት 30፤ 2013 በፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር በኩል እንዲያስገባ የሚያዝ ነው። የተከሳሽ ጠበቆች፤ ዐቃቤ ህግ የሚያቀርባቸው የደህንነት ስጋቶችን በተመለከተ መልሳቸውን ሰኔ 10፤ 2013 በችሎት በኩል እንዲያቀርቡም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)