በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፤ ገዢው ፓርቲ መራጮችን ከእውቅናቸው ውጪ አንድ ለአስር እንዲደራጁ በማድረግ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የተሞከረውን “በአለቃ የማስመረጥ ስርዓት ለመተግበር እየተፍጨረጨረ ነው” ሲል ወነጀለ። መራጮቹ የሚደራጁት “የብልጽግና ቤተሰብ” በሚል “የመጠርነፍ” አካሄድ መሆኑም አስታውቋል።
ተቃዋሚ ፓርቲው ይህን ያለው ዛሬ ግንቦት 19 ቀን 2013 ዓ.ም በዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ኢዜማ “ከፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት የሀገር ደህንነትና ቀጣይነት ይቀድማል” በሚል ርዕስ ለጋዜጠኞች ባሰራጨው መግለጫ ላይ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተፈጽመዋል ያላቸውን ህገ ወጥ አካሄዶች ዘርዝሯል።
“የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ‘የምርጫ ካርዳችሁን ለእኛ ስጡን ጊዜው ሲደርስ እንመልስላችኋለን’ በማለት፤ የመራጭነት ካርዶችን በመውሰድ፣ መራጮችን በማስፈራራት እና በማሳቀቅ ከምርጫው ሂደት ተገፍተው እንዲወጡ ጥረት እያደረገ ይገኛል” ሲል ኢዜማ በመግለጫው ከስሷል። ካድሬዎቹ “በራሱ ተነሳሽነት ለመመዝገብ የመጣውን እና ራሳቸው ከየቤቱ የሚያመጧቸውን አቅመ ደካማ መራጮች፤ የካርድ ቁጥራቸውን እና ስልክ ቁጥር በመመዝገብ ‘የምትመርጡትን እናውቃለን’ በሚል የማሸማቀቅ ስራ ውስጥ ገብተዋል’ በማለትም አክሏል።
ይህ አይነቱ ማስፈራሪያ በማህበረሰቡ ውስጥ በመዛመቱ፤ ዜጎች ምርጫው ነጻ መሆኑን እንዲጠራጠሩ እና ተሳትፏቸውም እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል ብሏል ኢዜማ። በመራጮች ምዝገባ ወቅት፤ ገዢው ፓርቲ ካድሬዎቹን በምርጫ ጣቢያ አካባቢ በማስቀመጥ “በምርጫ ቦርድ እና በብልጽግና ፓርቲ መካከል ልዩነት የለም” የሚል ምስል እንዲፈጠር አድርጓል ሲል የሚወነጅለው ኢዜማ፤ በዚህም ምክንያት ዜጎች “ ‘ብመርጥም ዋጋ የለውም፤ ለውጥ አያመጣም’ ብለው ራሳቸውን ከምርጫ እንዲያገልሉ ምክንያት ሆነዋል ብለን እናምናለን” ሲል ነቅፏል።
ኢዜማ በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሰረት “ትዕግስት እና ኃላፊነት የተሞላበት አካሄድ” መከተሉን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። ሆኖም ይህን አካሄዱን ገዢው ፓርቲ “እንደ ደካማነት” በመቁጠር፤ “በስልጣን ላይ ለመቆየት እና ምርጫውን እንደ ከዚህ በፊቱ የይስሙላ ቅቡልነት ማራዘሚያ ለማድረግ እኩይ ተግባራትን እየፈጸመ ነው” ሲል ጠንከር ባሉ ቃላት ወንጅሏል።
“ይህ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በአንድ በኩል ወደ ምርጫው ስንገባ ያስቀመጥናቸውን፤ ሊሟሉ የሚገቡ አነስተኛ መስፈርቶች በመናድ በምርጫው ላይ ያለንን ሀገርን የማሻገር እምነት በመሸርሸር፤ ሀገራችን አሁን ካለችበት ውስጣዊ እና ፈታኝ ውጫዊ ጫናዎች አንጻር፤ በተሳካ ሁኔታ የምርጫውን ሂደት ለመወጣት ያላትን ተስፋ እያደበዘዘው ይገኛል” ብሏል ኢዜማ።
ገዢው ፓርቲ ከአሁን በኋላ ከሚፈጽማቸው እኩይ ተግባራት እንዲቆጠብ እና የእርምት እርምጃዎች ላይ ተባባሪ እንዲሆን የጠየቀው ኢዜማ፤ “ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሀገርና በሕዝብ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት፤ የብልጽግና ፓርቲም እንደ ቀደሙ ገዥዎች ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጥም” ሲል አስጠንቅቋል።
ኢዜማ በመግለጫው እስካሁን ባደረገው የምርጫ እንቅስቃሴ ብዙ ችግሮች እንዳጋጠሙት ገልጿል። ፓርቲው አጋጠሙኝ ካላቸው ችግሮች መካከል በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በአባላቶቹ እና ደጋፊዎቹ ላይ የሚደርስ እስር እና ወከባ አንዱ ነው።
የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ስለዚሁ ጉዳይ ሲያብራሩ እንዳሉት፤ የኢዜማ አባላት “በከፍተኛ ሁኔታ እየተዋከቡ” ያሉት በአማራ እና ደቡብ ክልሎች ነው። በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን፤ ታች ጋይንት ወረዳ “እስከ ዛሬ ድረስ ስምንት አባሎቻችን እስር ቤት ነው የሚገኙት” የሚሉት አቶ ዋሲሁን፤ በዚያው ዞን ስር ባለችው አዲስ ዘመን ከተማ የፓርቲው ጽህፈት ቤት መዘጋቱን ተናግረዋል። በማዕከላዊ ጎንደር አላፋ ጣቁሳ እና በምስራቅ ጎጃም ዞን ፓርቲያቸው ከፍተኛ ችግር እንደገጠመውም አክለዋል።
በደቡብ ክልልም ተመሳሳይ ችግሮች እየደረሱባቸው መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ዋሲሁን፤ ክልሉን ለየት የሚያደርገው ግን የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የምርጫ ቅስቀሳ ለማካሄድ በሄዱባቸው ቦታዎች በአጠቃላይ “የኢዜማ አባላት በከፍተኛ ሁኔታ መታሰራቸው ነው” ባይ ናቸው። ፕሮፌሰር ብርሃኑ በሺህዎች በሚቆጠሩ ደጋፊዎች ታጅበው የምርጫ ቅስቀሳ ካካሄዱባቸው ቦታዎች መካከል የኮንሶ ዞን እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
“ኮንሶ ላይ 121 ሰው [ከግንቦት] 10 እስከ 13 ባለው ጊዜ ውስጥ ታስሮ አሁን የተፈቱት አርባ ሶስቱ ብቻ ናቸው። የተቀሩት አሁንም እስር ቤት ናቸው። ባስኬቶ ከተማ ላይ ዛሬ ብቻ 21 ሰው ታስሯል”
አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ- የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ
“ኮንሶ ላይ 121 ሰው [ከግንቦት] 10 እስከ 13 ባለው ጊዜ ውስጥ ታስሮ አሁን የተፈቱት አርባ ሶስቱ ብቻ ናቸው። የተቀሩት አሁንም እስር ቤት ናቸው። ባስኬቶ ከተማ ላይ ዛሬ ብቻ 21 ሰው ታስሯል” ብለዋል።
የታሰሩ ሰዎችን ዝርዝር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በየአካባቢው ለተቋቋሙ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጭምር ማሳወቃቸውን የሚገልጹት የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፤ ግን አንዱም ቦታ ላይ መፍትሄ አለማግኘታቸውን አስረድተዋል። “ይሄ ሁሉ እየተደረገ ባለበት፤ ምርጫው እንዴት አድርጎ ነው ዲሞክራሲያዊ ሊሆን የሚችለው? እንዴት አድርጎ ነው ፍትሃዊ ሊሆን የሚችለው? የሚለው እጅግ በጣም ያሳስበናል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)