አሜሪካ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች ልትጥል እንደምትችል አስጠነቀቀች

አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች ልትጥል እንደምትችል የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አስጠነቀቁ። የሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ ትናንት ሐሙስ በተደመጠበት የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ስብሰባ፤ ጂም ሪሽ የተባሉ ሴናተር ሀገራቸው በሰብዓዊ መብት ጥሰት የምትከሳቸውን ማዕቀብ በመጣል ለመቅጣት የምትጠቀምብትን “የማግኒትስኪ ድንጋጌ” እንድትጠቀም ጥቆማ ሰጥተዋል። 

በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረገው ውይይት ማብራሪያ የሰጡት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ሮበርት ጎዴክ “ግጭቱን የሚያባብሱ መንገዳቸውን ካልቀየሩ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተጨማሪ እርምጃ ይጠብቁ” ሲሉ ተደምጠዋል። ለሁለት ሰዓታት ገደማ በዘለቀው ውይይት የኢትዮጵያ ሽግግር፣ ምርጫ እና የህዳሴ ግድብ ድርድርን የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች የተነሱበት ይሁን እንጂ ቅድሚያውን የያዘው የትግራይ ውጊያ እና አሜሪካ ይህንኑ ለማስቆም የምታደርገው ጥረት ነበር። 

“እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አብዛኞቻችን ከአመታት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ሽግግር መካከል ትገኛለች ብለን በተስፋ እየተመለከተን ነበር” ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሊቀ-መንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ፤ ኢትዮጵያ “በመፍረስ ጎዳና ላይ ትገኛለች” ሲሉ ተደምጠዋል። ሴናተሩ ለደረሱበት ድምዳሜ በአስረጂነት የጠቀሷቸው፤ በኤርትራ ተሳትፎ “ዓለም አቀፋዊ መልክ ይዟል” ያሉትን የትግራይ ጦርነት፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ሁከቶች እና የጸጥታ መጓደልን እንዲሁም “የፖለቲካ ምህዳር በፍጥነት መዘጋት” ናቸው። 

ሴናተር ሜንዴዝ በመርሐ-ግብሩ መክፈቻ ላይ ባሰሙት በዚሁ ንግግራቸው በትግራይ እየሆነ ያለውን ከዚህ ቀደም በሱዳን ዳርፉር ከተከሰተው ጋር አወዳድረዋል። “የዘፈቀደ ግድያዎች፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ የትግራይ ሰዎችን በኃይል ማፈናቀል መኖራቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎች አሉ። ታጣቂ ኃይሎች የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ዘርፈዋል፤ አውድመዋል። የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን አጥቅተዋል” ብለዋል። 

የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ የምግብ ዕርዳታ ስርጭት በወታደሮች መታገዱን እንደዘገበ ጠቅሰው፤ “የግብረ ሰናይ ሰራተኞች ተገድለዋል፤ የትግራይ ሰዎች በዚህ ምክንያት ከጠኔ አፋፍ ይገኛሉ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ሴናተሩ “ሁሉም ወገኖች ጥፋተኞች ናቸው” ይበሉ እንጂ በተለይ፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም አጋር ያሏቸው ሚሊሺያዎች “በግዴለሽነት እና በጭካኔ ሰላማዊ ሰዎች ላይ አነጣጥረዋል” ሲሉ ወንጅለዋል።

ባለፉት አመታት በተከታታይ በተከሰቱ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የሰብል በሽታ እና የምግብ ዋጋ መናር ኢትዮጵያ ስትቸገር መቆየቷን የጠቀሱት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ኃላፊ ሳራ ቻርልስ፤ በትግራይ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። 

በትግራይ ያሉ ዜጎች በግጭት ምክንያት መገበያየት፣ ማሳቸውን ማረስ እና በርካታ አገልግሎቶች ማግኘት አለመቻላቸውን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ በዚህም የተነሳ ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን መመገብ መቸገራቸውን ለውጭ ግንኙነት ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል። በክልሉ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን እና 63,000 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን ተናግረዋል። 

በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች የምግብ እጥረቱ አስቸኳይ ከሚባልበት ደረጃ መድረሱን ገልጸው፤ በዚህ ደረጃ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ሰዎች “በምግብ እጥረት፣ በተመጣጠነ ምግብ እጦት፣ በበሽታ እና ረሃብ ለመሞታቸው የተረጋገጡ ሪፖርቶች እየደረሱን ነው” ብለዋል። ውጊያ ካልቆመ ኢትዮጵያ ባለፉት 40 ገደማ አመታት አይታው የማታውቀው ረሃብ ሊገጥማት እንደሚችልም ሳራ ቻርልስ አስጠንቅቀዋል። 

የትግራይ የጤና አገልግሎት አሁንም ባልቆመው ግጭት እና በዘረፋ ምክንያት ክፉኛ መጎዳቱን የገለጹት የUSAID ሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ኃላፊ፤  በክልሉ ከሚገኙ ሆስፒታሎች እና የጤና ማዕከሎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት የሚሰጡት 16 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል። “የተቀረው የትግራይ የጤና መሰረተ ልማት ተዘርፏል ወይም አልያም ሰዎች የሚፈልጉት አንገብጋቢ አገልግሎት ተከልክለው በታጣቂዎች ተይዟል” ብለዋል። 

በውይይቱ ላይ ጠንከር ያለ አቋማቸውን ካንጸባረቁት መካከል በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር የሆኑት ጂም ሪሽ አንዱ ናቸው። ሴናተሩ “ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲዊ ሽግግር የተገባው ቃል አሁንም ሊሳካ የሚችል ነው። ነገር ግን በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በቀጠናው የተፈጠሩ ክስተቶች እንዲሁም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ድንጋጤን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች የኢትዮጵያን ጉዞ አወሳስበውታል” ብለዋል። 

“በተለይ በትግራይ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መጻኢ እጣ ፈንታን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ ያላትን ተስፋ መሸርሸር ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሽግግር ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል ጥልቅ ስጋት ፈጥሯል” ብለዋል። 

ጦርነቱ በሱዳን እና በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን ማስተጓጎሉን፣ በኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች ውጥረት መቀስቀሱን የገለጹት ጂም ሪሽ፤ በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ሰበብ በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ የአካባቢው አገሮች ከአንዱ ለመወገን መገደዳቸውን በንባብ ባቀረቡት ንግግራቸው ለተሳታፊዎች ገልጸዋል። 

“በተለይ በትግራይ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መጻኢ እጣ ፈንታን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ ያላትን ተስፋ መሸርሸር ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ፖለቲካዊ ሽግግር ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል ጥልቅ ስጋት ፈጥሯል”

ጂም ሪሽ- በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር

ሴናተሩ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ግጭቱን ለማስቆም የ“ማግኒትስኪ ድንጋጌን” ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች እንዲጠቀም መክረዋል። የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትርም መንግስታቸውን ይኸንኑ ድንጋጌ ሊጠቀም እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል። 

ስለ ኢትዮጵያ ምርጫ የተጠየቁት ምክትል ሚኒስትሩ፤ በርከት ያሉ ችግሮች መኖራቸውን በሰጡት ምላሽ አብራርተዋል። “ስለ ፖለቲካ ምህዳሩም ስጋት አለ። ስጋታችንን ለመንግስት በግልጽ አሳውቀናል። አካታች ብሔራዊ ውይይት ያስፈልጋል። አንድ ምርጫ ችግሮችን ሁሉ አይፈታም። ስለተዓማኒነቱ ብርቱ ጥርጣሬዎች አሉ። በማህበረሰቦች መካከል ያሉ ውጥረቶችን ለመፍታት የረዥም ጊዜ ጥረት ለማየት እንፈልጋለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)