በቅድስት ሙላቱ
የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ገዢው ፓርቲ እያደረሰብኝ ነው ባለው ጫና ምክንያት መጪውን ምርጫ አቋርጦ ሊወጣ እንደሚችል አስጠነቀቀ። ዎሕዴግ በአባላቱ እና ደጋፊዎቹ ላይ ተፈጽመዋል ያላቸው የምርጫ ስነ ምግባር ጥሰቶች እና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በገለልተኛ አካል አጣርቶ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል።
ተቃዋሚ ፓርቲው ማስጠንቀቂያ እና ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ የመጪውን ሀገራዊ ምርጫ አፈጻጸም ሂደት በተመለከተ ትላንት ሐሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። ዎሕዴግ በዚሁ መግለጫው፤ በፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ላይ “ድብደባ እና አፈና” እየተፈጸሙባቸው ነው ሲል ወንጅሏል።
ከእነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪም የዎሕዴግ አባላት እና ደጋፊዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ትንኮሳዎች እንደሚገጥማቸው ፓርቲው በመግለጫው አንስቷል። የፓርቲው አባላት ትላንት ግንቦት 19፤ በሶዶ ዙሪያ ምርጫ ክልል 01፣ በባይራ ኮይሻ ወረዳ ከመራጩ ህዝብ ጋር ለመተዋወቅ በሄዱበት የገጠማቸውንም በማሳያነት ጠቅሷል። በዚሁ ወረዳ ለምርጫ ቅስቀሳ የተሰማሩ አባላቱ በፖሊስ ኃይል እገታ እና ድብደባ እንደደረሰባቸው እንዲሁም ለቅስቀሳ ሲጠቀሙበት ከነበረ መኪና እና ባነር ጋር ለእስራት መዳረጋቸውን አስቀምጧል።

ከዚህ በተጓዳኝ የፌደራል እና የክልል የመንግስት ባለስልጣናት ከህዝብ ጋር ተገናኝተው የምርጫ ቅስቀሳዎች በሚያደርጉበት ወቅት “ዛቻ እና ማስፈራሪያ የተሞላባቸው” አገላለጾችን እንደሚጠቀሙ ዎሕዴግ በመግለጫው ላይ አመላክቷል። እንደዚህ አይነት ቅስቀሳዎችም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ “የስህተት ትምህርት እየፈጠረ ነው” ሲልም አክሏል።
ዎሕዴግ ማስጠንቀቂያ ያዘለውን መግለጫ ለማውጣት የተገደደው፤ በፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለው “እስራት እና አፈና ከአቅሙ በላይ እየሆነ በመምጣቱ ነው” ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ጎአ ይናገራሉ። “የምርጫ ቅስቀሳ ከጀመርን ወዲህ የብልጽግና ጡንቻዎች ሲያርፉብን ቆይተዋል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት አቶ ጎበዜ፤ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለበርካታ ጊዜ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ መቅረቱን አስረድተዋል።
“አመራሮቻችን እና ዕጩዎቻችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከ30 ቀናት በላይ ይታሰራሉ” የሚሉት ሊቀመንበሩ፤ ፓርቲውን ለማዳከም እና የአባላቶቹን ሞራል ለመንካት ተደጋጋሚ ሙከራዎች መደረጋቸውን ይጠቁማሉ። ከ100 እስከ 200 የሚደርሱ አባላቶቻቸ በጸጥታ ኃይሎች በየጊዜው ታስረው እንደተለቀቁ የሚጠቅሱት አቶ ጎበዜ፤ እነዚህን መሰል “ኢ-ሰብዓዊ ጥቃቶች የምርጫ ስነ ምግባር ያላማከሉ ናቸው” ሲሉ ይተቻሉ።

በትላንትናው ዕለት በባይራ ኮይሻ ወረዳ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ በነበሩ የፓርቲው አባላቶች የተፈጸመውን እና በዎሕዴግ መግለጫ ላይ የተጠቀሰው ድርጊት እንዴት እንደተፈጸመም አብራርተዋል። “አራት ፓትሮል የፖሊስ መኪናዎች፤ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ ልጆችን ከብበው ደብድበዋል” በማለት የሚወነጅሉት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ “ሁለት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው አባላቶቻችን ገሱባ ሆስፒታል ተኝተዋል” ብለዋል። በወቅቱ ከተደበደቡት መካከል አንድ ሴት የክልሉ ዕጩ ተወዳዳሪ እንደምትገኝበትም ጠቁመዋል።
በትላንትናው የምርጫ ቅስቀሳ የታሰሩት አባላቶቻቸው 20 እንደሆኑ የሚገልጹት አቶ ጎበዜ፤ የቅስቀሳ መኪናቸው ጭምር እስካሁንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዳሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፓርቲው አመራሮች በዛሬው ዕለት ወደ ወረዳው ተጉዘው የታሰሩ አባላቶቻቸውን ለመጠየቅ ቢሞክሩም እንደተከለከሉም አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅትም ቦታው በጸጥታ አካላት ተከብቦ እንዳለ ጨምረው ጠቅሰዋል።
እንደዚህ አይነት ድርጊቶች የሚቀጥሉ ከሆነ፤ ፓርቲው አካሄዶችን ገምግሞ ለአባላቱ እና ለወላይታ ህዝብ ደህንነት ሲል ከምርጫ እራሱን እንደሚያገል አቶ ጎበዜ አስጠንቅቀዋል። ትላንት ምሽት የወጣው የፓርቲው መግለጫም ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቋል። በወላይታ ዞን የሚስተዋሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች የማይታረሙ ከሆነ ዎሕዴግ ሳይወድ በግድ ምርጫውን ለቆ እንደሚወጣ በአቋም መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

“የፓርቲው ሊቀመንበር እኔ ነኝ” የሚሉት አቶ ተክሌ ቦረና ግን የአቶ ጎበዜንም ሆነ በፓርቲው መግለጫ የተጠቀሰውን ማስጠንቀቂያ አይቀበሉም። “ዎሕዴግ እየደረሱ ያሉበትን ችግሮች ተቋቁሞ ምርጫውን ይወዳደራል እንጂ ለቅቆ ሊወጣ አይችልም” ያሉት አቶ ተክሌ፤ “ምርጫውን ለቆ ለመውጣት እንደተገደደ የሚል መግለጫ ለውሳኔ አይበቃም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አቶ ተክሌ “ሊቀመንበሩ እኔ ነኝ” ማለታቸውን አቶ ጎበዜ አስተባብለዋል። ግለሰቡ ከዚህ በፊት የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩ ቢሆንም ከጥር 1፤ 2013 ጀምሮ ግን በፓርቲው ውሳኔ መሰረት በምክትል ሊቀመንበርነት እንዲያገለግሉ ተመድበው ነበር ብለዋል። ሆኖም በምክትል ሊቀመንበርነት ለማገልገል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እና ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ እየተወጡ ባለመሆኑ ከመጋቢት ወር አንስቶ ከፓርቲ አመራርነት መታገዳቸውን አብራርተዋል።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የፓርቲው አባል ይህንኑ ገለጻ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “አሁን ፓርቲውን በሊቀ መንበርነት እየመሩ ያሉት አቶ ጎበዜ ናቸው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)