ምርጫ ቦርድ የባልደራስ አመራሮችን በዕጩነት የመመዝገብ ሂደት መጀመሩን አስታወቀ

በሃሚድ አወል

አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችን በዕጩነት የመመዘገብ ሂደት መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ የፓርቲው አመራሮች ለሚወዳደሩባቸው ቦታዎች፤ ቀደም ሲል አሳትሟቸው የነበሩትን ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲቃጠሉ ትዕዛዝ ማስተላለፉንም ገልጿል።  

ቦርዱ ይህን የገለጸው ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 26 ላስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለችሎቱ እንደተናገሩት፤ የባልደራስ ፓርቲ ቀደም ሲል አስመዝግቧቸው በነበሩ ዕጩዎች ምትክ ለምርጫ እንዲቀርቡለት የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች እንዲያሳውቅ በመስሪያ ቤታቸው በኩል ጥያቄ ቀርቦለታል። በዚህም መሰረት ፓርቲው በትላንትናው ዕለት አዲሶቹን ዕጩዎች ማሳወቁን አስረድተዋል።

ይህንን የቦርዱን ሰብሳቢ ገለጻ የባልደራስ ፓርቲ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለፍርድ ቤቱ አረጋግጠዋል። ምርጫ ቦርድ የዕጩዎችን ምዝገባ ለመፈጸም እንዲያስችለው፤ ባልደራስ በተተኪነት የሚያቀርባቸውን ዕጩዎች ፎቶግራፎች እንዲያቀርቡ መጠየቁን ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። በጥያቄው መሰረትም የዕጩዎችን “ፎቶግራፎች ለቦርዱ ሰጥተናል” ያሉት አቶ ሄኖክ፤ ሆኖም “ማረጋገጥ የምንችለው የዕጩዎች ሰርተፊኬት ስንቀበል ነው” ብለዋል።

“የዕጩዎች ሰርተፊኬት የመስጠት ሂደት ቦርዱ በ30 ደቂቃ ማከናወን የሚችለው ነገር ነው። ነገር ግን ቦርዱ ይህን ማድረግ አልቻለም” ሲሉ የባልደራስ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የዕጩዎች ሰርተፊኬት የመስጠት ሂደት በምን ያህል ጊዜ ሊያልቅ እንደሚችል በፍርድ ቤቱ የተጠየቁት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፤ “ነገ ጠዋት ያልቃል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

የቦርድ ሰብሳቢዋ መስሪያ ቤታቸው ከዕጩዎች ምዝገባ ባሻገር የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ለማስፈጸም ያከናወነውን ተግባር ለፍርድ ቤት አብራርተዋል። የባልደራስ ፓርቲ የታሰሩ አመራሮቹን በዕጩነት አስመዘግብባቸዋለሁ ላላቸው ቦታዎች ቦርዱ ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ቀደም ብሎ አሳትሞ መጨረሱን ብርቱካን በማብራሪያቸው አስታውሰዋል። 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእስር ላይ ያሉ የባልደራስ አመራሮች ለምርጫ በዕጩነት መቅረብ እንደሚችሉ በግንቦት 16 ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ግን ቦርዱ የታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን እንዲቃጠሉ እና በሌላ እንዲተኩ ሂደቱን መጀመሩን ሰብሳቢዋ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን የሚያትመው ኩባንያም ይህንን ሂደት በሶስት እና አራት ቀናቶች ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ማስታወቁንም በማብራሪያቸው አንስተዋል። ይህ አጠቃላይ ሂደት ቦርዱን ተጨማሪ 3.5 ሚሊዮን ብር እንደሚያስወጣውም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ባልደራስ በእስር የሚገኙ አራት አመራሮቹን በዕጩነት ለማስመዘገብ ጠይቆ በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ሳይገኝ ከቀረ በኋላ፤ በእነርሱ ምትክ ሌሎች አባላቱን አስመዝግቦ ነበር። እነዚህ ተተኪ ዕጩዎች በየካ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራንዮ እና አቃቂ ቃሊቲ የምርጫ ክልሎች ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለመወዳደር በምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ቆይተዋል። 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ውድቅ ካደረገ በኋላ ግን በእነዚህ የምርጫ ክልሎች የተመዘገቡ አራት ዕጩዎች በእስር ላይ በሚገኙት የባልደራስ አመራሮች ተተክተዋል። የባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ የተኳቸው በየካ ምርጫ ክልል የተመዘገቡትን አቶ አለማየሁ አበበን መሆኑን የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የፓርቲው የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በሚወዳደሩበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ የምርጫ ክልል ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለውድድር የቀረቡት አቶ ደምሌ አባተ እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ዕጩነታቸውን ማስረከባቸውን ምንጮች ገልጸዋል። የባልደራስ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ አስካለ ደምሌ ለዕጩነት በቀረቡበት በኮልፌ ቀራንዮ ምርጫ ክልል ከተወዳዳሪነት የተሰናበቱት አቶ ይልቃል ሙሉዬ መሆናቸውን ከፓርቲው ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እንደ ሶስቱ አመራሮች ሁሉ በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል ቀለብ (አስቴር) ስዩም አቶ ንጉሴ ደርበውን ተክተው ለምርጫ እንደሚወዳደሩ ምንጮች አክለዋል። 

ምርጫ ቦርድ የእነ እስክንድር ነጋን የዕጩነት ምዝገባ ሂደት እያስፈጸመ መሆኑን በዛሬው የችሎት ውሎ ቢገልጽም፤ ባለፈው ሳምንት ግንቦት 18 ለባልደራስ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ ግን በእስር ላይ ያሉትን አባላቱን በተመለከተ በሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም እንደሚቸገር አስታውቆ ነበር። ቦርዱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት በላከው ባለ አምስት ገጽ የአፈጻጸም ማብራሪያ ላይም “ፓርቲው ቀደም ብሎ ያስመዘገባቸውን ዕጩዎች መሰረዝ እንደሚያዳግተው” ማስታወቁ አይዘነጋም። 

ቦርዱ በዚሁ ማብራሪያው ላይ የሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔን ለመፈጸም የሚቸገርባቸውን ምክንያቶች አቅርቧል። አንደኛው የቦርዱ ምክንያት በቦርዱ ላይ የተጣለ ህጋዊ የጊዜው ገደብ መኖር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የምርጫ ዝግጅት በመጠናቀቁ እንደዚህ አይነት ውሳኔን ተግባራዊ ለማድረግ “አፈጻጸሙን አዳጋች ያደርገዋል” በሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪም “አፈጻጸሙ በሌሎች ዜጎች መብቶች ላይ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ” ቦርዱ በምክንያትነት አንስቷል።  

ባልደራስ የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ በደረሰው በማግስቱ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስገባው አቤቱታ፤ የፓርቲው ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የመጪው ምርጫ የድምጽ መስጪያ ቀን እንዲታገድ ጠይቆ ነበር። የእግድ ጥያቄው የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህንኑ ጉዳይ በዛሬው የችሎት ውሎው አንስቶት ነበር። የባልደራስ ፓርቲ ጠበቃ አቶ ሄኖክ፤ ምርጫ ቦርድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን መፈጸም በመጀመሩ ፓርቲያቸው ያቀረበውን ጥያቄ እንደማይቀጥልበት ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል።

የፓርቲውን እና የምርጫ ቦርድን ምላሾች ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ትዕዛዝ እና ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱን ውሎ አጠናቋል። ፍርድ ቤቱ ለዕጩ ተወዳዳሪዎች ሰርተፊኬት መስጠት እና ሌሎች የአፈጻጸም ስራዎች ተጠናቅቀው ለመጪው ሰኞ ግንቦት 30 እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)