ኢዜማ አዲስ አበባን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ ከነዋሪዎች ጋር ሊወያይ ነው

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የአዲስ አበባ ከተማን በተመለከተ በሚያራምዳቸው አቋሞች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን አስታወቀ። ነገ ቅዳሜ ግንቦት 28 በአዲስ አበባው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በሚደረገው በዚሁ ውይይት ላይ የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ሌሎችም የፓርቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደሚገኙም ገልጿል። 

የቅዳሜው የውይይት መድረክ ፓርቲው በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ካደረጋቸው ህዝባዊ ውይይቶች ጋር “በይዘት ተመሳሳይ” መሆኑን የሚናገሩት የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ክፍል የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ፤ ዋና ዓላማው “አዲስ አበባን አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎችን ግልጽ ማድረግ ነው” ብለዋል። “ኢዜማን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በርካታ አጀንዳዎች ይዘዋወራሉ” የሚሉት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው፤ በነገው ውይይትም ፓርቲውን የተመለከቱ ጥያቄዎች በተሳታፊዎች ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። 

እስከ 500 የሚገመቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው በቅዳሜው ውይይት ላይ ያነጋግራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል አንዱ የቀበሌ ቤቶች ጉዳይ ነው። ኢዜማ ባለፈው መጋቢት ወር ይፋ ባደረገው የአዲስ አበባ የምርጫ ማኒፌስቶ ላይ በከተማዋ የሚገኙ የቀበሌ ቤቶችን ከመንግስት ወደ ነዋሪዎቹ በሽያጭ ለማዘዋወር የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር።

“በከተማዋ የሚገኙ የቀበሌ ቤቶችን የከተማ አስተዳደሩ የሚያወጣቸውን የጥራት ደረጃዎች መሰረት ባደረገ መልኩ፤ በቤቶቹ ለሚኖሩት ቅድሚያ በመስጠት የቤቶቹን ባለቤትነት በሁለት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከመንግስት ወደ ነዋሪዎቹ በሽያጭ ለማዘዋወር የሚያስችል አሰራር ቀይሰን ተግባራዊ እናደርጋለን” ሲል ፓርቲው  ለአዲስ አበባ ባዘጋጀው ሰነድ ቃል ገብቷል።   

ይህ የፓርቲው ዕቅድ የከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎችን ግራ እንዳጋባ የኢዜማ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ይቀበላሉ። “ቃል የገባናቸው ጉዳዮች ላይ የአፈጻጸም ጥያቄ ያላቸው ህዝቦች አሉ። እነሱ ላይ ማብራሪያ እንሰጣለን” ሲሉ ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በቅዳሜው የውይይት መድረክ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተጨማሪ አራት የኢዜማ የምርጫ ዕጩዎች ይገኛሉ።  ከዕጩዎቹ መካከል ኢዜማን ወክለው ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ ክቡር ገና ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)