በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ስድስት የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂዎች ተገደሉ

በሃሚድ አወል

ስድስት የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በቤንች ሸኮ ዞን በሚገኘው ጉራፈርዳ ወረዳ ውስጥ በትላንትናው ዕለት መገደላቸውን አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የልዩ ኃይል አባላቱ የተገደሉት በወረዳው ስር ባለው ወጀምታ ቀበሌ እንደሆነም እኚሁ ባለስልጣን ገልጸዋል። 

ጥቃት የተፈጸመባቸው የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት፤ በወጀምታ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሰንበሊጥ በተባለ ቦታ ባለ ካምፕ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ መሆናቸውን የጉራፈርዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ሻሎም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ስምንት የልዩ ኃይል አባላት፤ ትላንት አርብ ግንቦት 27 ጠዋት ሁለት ሰዓት ገደማ፤ አንድ የካምፑን ሰራተኛ አጅበው ውሃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ ሲሄዱ ተኩስ እንደተከፈተባቸው አስረድተዋል። 

በጥቃቱ ስድስት የልዩ ኃይል አባላት ሲገደሉ አብሯቸው የነበረው የካምፑ ሰራተኛ ጉዳት ደርሶበት ህክምና ላይ ይገኛል ብለዋል። ለአጀባ ከተሰማሩት የጸጥታ ኃይሎች ውስጥ ሁለቱ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸውም አክለዋል። 

በጉራፈርዳ የሚገኙ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት እና ሚሊሻዎች ከወረዳው በተሰጣቸው ስምሪት መሰረት ለአምስት ቀናት “ኦፕሬሽን” ላይ እንደነበሩ የጠቆሙት አቶ ሲሳይ፤ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ወደ ካምፕ በተመለሱ በሁለተኛ ቀናቸው እንደሆነ አመልክተዋል። የጸጥታ ኃይሎቹ በዚሁ ስምሪታቸው “የታጠቁ ኃይሎች ይገኙባቸዋል” የተባሉ ጫካዎችን ሲያስሱ እንደነበር እና “በተወሰኑት ላይ እርምጃ እንደወሰዱም” አብራርተዋል።  

የጸጥታ ኃይሎቹ ከስምሪት እንዲመለሱ የተደረጉት፤ የደቡብ ክልል ከፍተኛ የጸጥታ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 28 “የኦፕሬሽን ግምገማ ለማካሄድ” ታስቦ እንደነበር የጉራፈርዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አስረድተዋል። ጥቃቱን ስለፈጸሙ ታጣቂዎች ማንነት የተጠየቁት አስተዳዳሪው፤ “የተደራጁ ኃይሎች ናቸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።  

“እከሌ ነው ብለህ አታውቀውም። ከተደራጁ ስድስት፤ ሰባት ወራቸው ነው። ቦታ እየቀያየሩ ነው ጥቃት የሚያደርሱት” ሲሉ አቶ ሲሳይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በጉራፈርዳ ወረዳ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎችም ሲፈናቀሉ ቆይተዋል። በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ታጣቂዎች በአካባቢው በፈጸሙት ጥቃት የ31 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ አምስት ሰዎች የአካል ጉዳት እንደረሰባቸው መገለጹ ይታወሳል። በዚሁ ጥቃት 1,500 አባወራዎች መፈናቀላቸው በወቅቱ ተዝግቧል። 

በአካባቢው የሚፈጸመው ጥቃት በዚህ ወርም መቀጠሉን የወረዳው ነዋሪዎች ከሳምንት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። በወረዳው ግንቦት 14 በተፈጸመው ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ታጣቂዎቹ ግንቦት 16 እና 17 በተከታታይ በሰነዘሩት ጥቃት በድምሩ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የሚገልጹት የወረዳው ነዋሪዎች፤ ጥቃቶቹን ተከትሎም በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስረድተዋል። ተፈናቃዮቹ የዞኑ ዋና ማዕከል በሆነችው በሚዛን ተፈሪ እና በኩጃ ከተሞች ተጠልለው እንደሚገኙም አክለዋል። 

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ሳጅን አየለ፤ በግንቦት 16 እና 17 በጉራፈርዳ ወረዳ ጥቃት መፈጸሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠው ነበር። በሁለቱ ቀናት በነበረው ጥቃት በድምር የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የሚናገሩት የፖሊስ አዛዡ፤ ሆኖም “የተጎዳ ሰው አለ የሚባለው ግን ሀሰት ነው” ሲሉ አስተባብለዋል። 

“በእኛ በኩል በተደጋጋሚ የጸጥታ ኃይል እንዲጨመር፤ መከላከያ ሰራዊትም እንዲገባ ጠይቀናል…ታጣቂው ኃይል በጣም የተደራጀ ስለሆነ መቆጣጠር አልተቻለም”

አቶ ሲሳይ ሻሎም – የጉራፈርዳ ወረዳ አስተዳዳሪ

ጥቃት ፈጻሚዎቹ “ማንነታቸው የማይታወቅ ጸረ-ሰላም ኃይሎች” ናቸው የሚሉት የፖሊስ አዛዡ፤ “ጥቃት ካደረሱ በኋላ ወደ ጫካ ስለሚገቡ ጥቃት አድራሾችን በቁጥጥር ስር ለማዋል አልተቻለም” ሲሉም በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር አስረድተው ነበር። የጉራፈርዳ ወረዳ አስተዳዳሪም የአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ “ከወረዳው አቅም በላይ ነው” ሲሉ የፖሊስ አዛዡን ገለጻ ያጠናክራሉ። 

“በእኛ በኩል በተደጋጋሚ የጸጥታ ኃይል እንዲጨመር፤ መከላከያ ሰራዊትም እንዲገባ ጠይቀናል” የሚሉት አቶ ሲሳይ፤ ከወረዳው ጥያቄ በኋላ የጸረ-ሽብር እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ቁጥር እንደተጨመረ ተናግረዋል። እንዲያም ቢሆን ግን “ታጣቂው ኃይል በጣም የተደራጀ ስለሆነ መቆጣጠር አልተቻለም” ብለዋል። 

የጉራፈርዳ ወረዳ አስተዳዳሪ የአካባቢያቸውን ሁኔታ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስር ካለው የመተከል ዞን ጋር ያመሳስሉታል። በወረዳው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢነት በአጽንኦት የሚገልጹት አስተዳዳሪው፤ ሁኔታው “ከወረዳውም ከዞኑም አቅም በላይ ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የትላንትናውን ጥቃት በተመለከተ ከጉራፈርዳ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ እና ከቤንች ሸኮ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። 

የጉራፈርዳ ወረዳ በሚገኝበት ቤንች ሸኮ ዞን በጸጥታ ኃይሎች ላይ ግድያ ሲፈጸም የአሁኑ በወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት ግንቦት 9 በሸኮ ወረዳ በአይበራና ሳንቃ ቀበሌ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ስድስት የልዩ ኃይል እና ሶስት የመደበኛ ፖሊስና አባላት መገደላቸውን ዞኑ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። በዚሁ ጥቃት ሶስት የጸጥታ ኃይል አባላት መቁሰላቸውም ተነግሯል። ጥቃቱን ተከትሎ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄዱት የሸኮ ወረዳ እና የቤንች ሸኮ ዞን ምክር ቤቶች ጥቃቱን በጽኑ ማውገዛቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)