በሃሚድ አወል
ዛሬ ግንቦት 28 ነው። ነገሮች በታቀደላቸው መልኩ ተከናውነው ቢሆን ኖሮ የዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ አስራ አንደኛ ክልል የውልደት ቀን ይሆን ነበር። ዛሬ እንዲደረግ ቀን ተቆርጦለት በነበረው ህዝበ ውሳኔ አስራ አንደኛውን ክልል ለመመስረት የተሰባሰቡት፤ በደቡብ ክልል የሚገኙ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ናቸው። ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጎን ለጎን የሚካሄደው ይህ ህዝበ ውሳኔ ለሁለት ሳምንት በተራዘመበት በዚህ ወቅት የአዲሱ ክልል ምስረታ ዝግጅት አሁንም አለመጠናቀቅ ግን አጠያያቂ ሆኗል።
የዝግጅት ስራው እየተከናወነ የሚገኘው “የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች የህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚ ኮሚቴ” በሚል ስያሜ በተዋቀረ ቡድን ነው። ኮሚቴው በስሩ የህዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትን አደራጅቶ ወደ ስራ የገባው በየካቲት 2013 ነበር። ስድስት አባላት ያሉት ይህ ጽህፈት ቤት አዲሱን የክልል ምስረታ የተመለከቱ አብዛኞቹን ስራዎች እያከናወነ ያለ ነው።
በደቡብ ክልል እውቅና የተደራጀው ይህ ጽህፈት ቤት ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል ክልሉ ከተመሰረተ በኋላ ሊኖረው የሚገባውን ህገ መንግስት እና ሌሎች የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ይገኝበታል። የደቡብ ምዕራብ ክልል ህዝበ ውሳኔ አደራጅ ዐብይ ኮሚቴ እና ቴክኒክ ኮሚቴ፤ ባለፈው ሚያዚያ ወር በሻሸመኔ ከተማ ባካሄዱት የስራ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ፤ የህግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ከሚያዚያ 12 እስከ ሚያዚያ 30 ባለው ጊዜ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ተወስኖ ነበር። ሆኖም የክልሉ ስያሜ፣ የስራ ቋንቋ፣ ሰንደቅ አላማ እና የክልሉ መንግስት መቀመጫ ከተማን የሚወስኑት የህገ መንግስቱ ክፍሎች አሁንም አለመጠናቀቃቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያገኘችው መረጃ ያሳያል።
የተጓተተው የህገ መንግስት ሰነድ ዝግጅት
በህዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት፤ የህገ መንግስት እና ሌሎች የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት ግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ አበበ ወልዴ፤ የረቂቅ ህገ መንግስቱ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ረቂቅ ህገ መንግስቱን የሚያዘጋጁት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከፍትህ አካላት የተውጣጡ አስራ ሁለት የህግ ባለሙያዎች መሆናቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል።
በቴክኒክ ኮሚቴ የሚዘጋጀው ረቂቅ የክልሉ ህገ መንግስት በሁለት መልኩ ለውይይት ይቀርባል ተብሎ እቅድ ተይዞለታል። ሙሉው የህገ መንግስት ረቂቅ ሰነድ ለውይይት የሚቀርበው “አማካሪ ካውንስል” ተብሎ ለሚጠራው አካል ነው። በረቂቅ ህገ መንግስቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ በጠቅላላ ድንጋጌዎች ስር የሚሰፍሩ መሰረታዊ ክፍሎችን የተመለከቱ ውይይቶች ደግሞ ከህዝብ ጋር የሚደረግ ነው።
የህገ መንግስት ረቂቁ ለ“አማካሪ ካውንስል” ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ቢባልም የካውንስሉ አባላት እስካሁንም አልተመረጡም። የአማካሪ ካውንስል አባላቱ ከሳምንት በኋላ እንደሚመረጡ እና ከዚያ በኋላ ውይይት እንደሚደረግ አቶ አበበ ይናገራሉ። የህዝበ ውሳኔ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው የረቂቅ ህገ መንግስቱ መሰረታዊ ክፍሎች ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ በአካባቢው ህዝብ ውይይት እንደሚደረግባቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
መሰል ውይይቶች በአምስቱ ዞኖች እና በልዩ ወረዳ ደረጃ ቀድመው መደረጋቸውን አቶ ጸጋዬ ገልጸዋል። ከደቡብ ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል ለመመስረት የተሰባሰቡት አምስት ዞኖች ምዕራብ ኦሞ፣ ቤንች ሸኮ፣ ካፋ፣ ዳውሮ እና ሸካ ዞኖች ናቸው። የኮንታ ልዩ ወረዳም የዚሁ የአዲስ ክልል ምስረታ ስብስብ አካል ነው።
ቀደም ሲል ህዝበ ውሳኔው ይካሄድበታል እስከተባለበት ግንቦት 28 ድረስ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የህዝብ ውይይት አለመካሄዱ፤ “ከህዝበ ውሳኔው በኋላ ያለውን ክልሉን የማደራጀት ስራ ላይ መዘግየትን አይፈጥርም ወይ?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ጸጋዬ የሲዳማን ጉዳይ በማጣቀስ ምላሽ ሰጥተዋል። “ከዚህ በፊት ከነበረው የሲዳማ ህዝብ ውሳኔ በመነሳት፤ ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ የምርጫ ውጤትን ይፋ ለማድረግ እስከ አስራ አምስት ቀናት ይወስድበታል። ስለሆነም ጊዜ ይኖረናል” ብለዋል።
ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ በሚኖሩት ቀናት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዝግ መሆኑ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚሰጣቸውም ያስረዳሉ። “የስልጣን ርክክቡ ሊካሄድ የሚችለው ከሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር በኋላ ነው” የሚሉት አቶ ጸጋዬ፤ ይህም በረቂቅ ህገ መንግስቱ ላይ ለሚካሄዱት ውይይቶች በቂ ጊዜ እንዲኖር ያስችላል ይላሉ።
ያልተኮረጀው የ10ኛው ክልል ተሞክሮ
እርሳቸውን ይህን ይበሉ እንጂ የአዲስ ክልል ምስረታ ሂደት፤ በተመሳሳይ የህዝበ ውሳኔ አካሄድ አስረኛ የኢትዮጵያ ክልል ከሆነው ሲዳማ ጋር ሲነጻጸር እንኳ ጉልህ መዘግየቶች ይታዩበታል። ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት ለመደራጀት ጥያቄውን በይፋ ካቀረበበት ከሐምሌ 11፤ 2010 ጀምሮ በአፋጣኝ ወደ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች መግባቱን በሂደቱ የተሳተፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የቅድመ ዝግጅቱ ዋና አካል የህገ መንግስት ረቂቅ እና ሌሎች ተያያዥ የህግ ማዕቀፎች ማዘጋጀት እንደነበርም ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ።
የሲዳማ ክልል ረቂቅ ህገመንግስት 95 በመቶው የተጠናቀቀው ህዝበ ውሳኔ ከመካሄዱ በፊት እንደነበር በክልሉ ህገ መንግስት ዝግጅት ላይ ተሳትፎ የነበራቸው አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። “የህገ መንግስት እና የሌሎች የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት ቀድሞ መጠናቀቅ፤ ከሲዳማ ህዝበ ውሳኔ በኋላ የነበረውን ክልል የማዋቀር ስራ አቅልሎታል” ይላሉ የዩኒቨርስቲው መምህር።
የሲዳማ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ማቶ ማሩ በመምህሩ አስተያየት ይስማማሉ። “የሲዳማ ክልል ከምስረታ በኋላ የተረጋጋ የሆነበት ምክንያት፤ የሰነድ ስራዎች ቀድመው ስላለቁ ነው። ከህዝበ ውሳኔው በኋላ በቀጥታ ክልሉን ወደ ማደራጀት ነው የሄድነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ሰኔ 14 የሚካሄደውን ህዝበ ውሳኔ እየጠበቀ የሚገኘው አዲስ ክልል የህገ መንግስት ማዘጋጀት ስራውን ቀድሞ ቢጀምርም በሰነዱ የሚካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች እስካሁንም እልባት አለማግኘታቸው ጥያቄዎች አጭሯል። የክልል ስያሜ፣ የስራ ቋንቋ፣ ሰንደቅ ዓላማ እና የዋና ማዕከልን መሰየም በማሳየነት የሚነሱ ናቸው። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እስካለፈው ሳምንት ድረስ የተላለፈ ውሳኔ እንደሌለ በህዝበ ውሳኔ አስተባባሪ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት፤ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ለሆኑት አቶ እሸቱ ገብረ ማርያም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የስራ ቋንቋ በተመለከተ በህገ መንግስት ረቂቁ ላይ እስካሁን የተወሰነ የስራ ቋንቋ እንደሌለ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪው ይናገራሉ። አዲስ በሚቋቋመው ክልል አንድ የስራ ቋንቋ እንደሚኖር የጠቆሙት አቶ እሸቱ፤ ረቂቅ ህገ መንግስቱ ህዝቦች የራሳቸውን ቋንቋ እና ባህል እንዲያሳድጉ ያበረታታል ብለዋል። በአካባቢው ከአስራ ሶስት በላይ ቋንቋዎች ይነገራሉ የሚሉት የህዝበ ውሳኔ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጸጋዬ፤ አንዱ ህዝብ የሌላውን ቋንቋ ስለማይናገር አማርኛ የክልሉ የስራ ቋንቋ ሊሆን ይችላል ሲሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
የአዲሱ ክልል ማዕከል የት ይሆናል?
የማዕከልን ጉዳይ በተመለከተ በህገ መንግስት ረቂቁ ላይ እስካሁን በግልጽ የሰፈረ ነገር ባይኖርም፤ ከአንድ በላይ ማዕከል ይኖራል የሚል መግባባት እንዳለ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪው ይገልጻሉ። ነገር ግን ክልሉ ምን ያህል ማዕከላት እንደሚኖሩት እና የትኛው ከተማ የክልሉ ማዕከል እንደሚሆን የሚወስነው ከህዝበ ውሳኔ በኋላ የሚቋቋመው የክልሉ ምክር ቤት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ከአንድ በላይ ማዕከላትን ማበጀት የክልሉ ነዋሪዎች ለሁሉም አገልግሎት ወደ አንድ ማዕከል የሚያደርጉትን እንግልት እንደሚቀንስ እና አንዳንድ አገልግሎቶችን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ እንደሚስችላቸው የፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አባላቱ ይናገራሉ። አቶ እሸቱ ግን “የትኛውም ከተማ በማዕከልነት ቢመረጥ ልዩነት አይኖረውም። ከተሞች ማዕከል በመሆናቸው ብቻ ተለይተው የሚያድጉበት ሁኔታ አይኖርም” ሲሉ የማዕከልነት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው አጀንዳ እንዳልሆነ ለማሳመን ይሞክራሉ።
የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪው የማዕከልነት እና የዋና ከተማነት ጉዳይ ቢያቃልሉትም፤ ለአዲሱ ክልል ምስረታ ዐቢይ ከሚባሉ ገፊ ምክንያቶች መካከል አንዱ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ መሆኑን የአካባቢውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ። በ“ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ” ስብስብ ስር ካሉት የአስተዳደር መዋቅሮች መካከል የካፋ እና የቤንች ሸኮ ዞኖች በተለይ የዋና ከተማ ርቀት ጉዳይ የሚያሳስባቸው ናቸው። የሁለቱ ዞኖች አመራሮች አካባቢያቸው ከደቡብ ክልል ዋና ማዕከል ከሆነችው ሃዋሳ ያላቸው ርቀት “በጣም ረዥም” በመሆኑ ምክንያት፤ አብዛኛውን ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን የሚያጠፉት በጉዞ ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ተደምጠዋል።
ከርቀቱ በተጨማሪ፤ አካባቢው በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ ሆኖ ሳለ ከሌሎች የደቡብ ክልል አካባቢዎች ጋር ሲነጻጸር ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል አለማግኘቱ እና በአካባቢው ያለው የልማት ተደራሽነትም አነስተኛ መሆኑ ለክልል ምስረታ ጥያቄ በልሂቃኑ እንደምክንያት ይነሳል። በጋራ ክልል እንዲደራጁ በምክር ቤቶቻቸው ከወሰኑት መካከል አንዱ የሆነው የኮንታ ልዩ ወረዳ፤ በገበታ ለሃገር እንዲለሙ ከታጩት ቦታዎች መካከል አንዱ የሆነው የኮይሻ አካባቢ መገኛ ነው። የኦሞ ብሄራዊ ፓርክም መገኛው በምዕራብ ኦሞ ዞን ውስጥ ነው፡፡
ከደቡብ ምዕራብ ህዝቦች የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ “እነዚህ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በምን መለኪያ እና በማን አነሳሽት ነው በአንድ ክልል ለመደራጀት የወሰኑት? የሚለው ጥያቄ ይነሳል። የህዝበ ውሳኔ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ በድሩ፤ የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳው ምክር ቤቶች በተናጠል ባካሄዱት መደበኛ ጉባኤ በአንድ ክልል እንዲደራጁ የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ስለማጽደቃቸው ይናገራሉ።
የምክር ቤቶቹ ውሳኔዎች እንደ እንግዳ ነገር መወሰድ የለበትም ሲሉ የአካባቢውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ታዛቢ ይከራከራሉ። ለዚህም በማሳያነት የሚጠቅሱት እነዚህ አካባቢዎች በቀድሞው አስተዳደር የከፋ ጠቅላይ ግዛት ተብለው በአንድ የአስተዳደር መዋቅር ስር የነበሩ ህዝቦች እንደነበሩ ነው። ከደርግ መንግስት በኋላ ተቋቁሞ በነበረው ሽግግር መንግስትም ክልል 11 በሚል ስያሜ ከፋ፣ ቤንች ማጂ እና ሸካ በአንድ ክልል ስር ተዋቅረው እንደነበርም መለስ ብለው ያስታውሳሉ። የአምስቱ ዞኖች እና ልዩ ወረዳው ኩታ ገጠምነትም በአንድ ክልል ስር ለመደራጀት እንዲወስኑ እንዳደረጋቸው ያስረዳሉ።
ክልል 11ን ጨምሮ አምስት ራሳቸውን ችለው ተደራጅተው የነበሩ ክልሎች፤ አሁን “የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል” በሚል በሚታወቀው ክልል ስር እንዲዋቀሩ የተደረገው በ1987 ነው። ይህን ክልሉን በአንድ የማምጣት ውሳኔ “በፌደራል መንግስት በዘፈቀደ የተወሰነ ውሳኔ እና የነዋሪዎችን ፍቃድ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” የሚል ትችት ይቀርብበታል። ይህንን ትችት የቀድሞው የክልሉ ገዢ ፓርቲ ደኢህዴን አይቀበለውም። ደኢህዴን “የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የአደረጃጀት ጥያቄዎች መንስኤ እና የመፍትሄ አቅጣጫ” በሚል ርዕስ አስጠናሁት ባለው ጥናት፤ የ1987 የደቡብ ክልል አወቃቀር “በዘፈቀደ የተወሰነ አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)