ኢዜማ በአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ላይ “የማመቻመች አቋም” እንደሌለው አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ላይ “ምንም አይነት ብዥታ” እንደሌለው እና በጉዳዩ ላይም “የማመቻመች አቋም” እንደማይከተል አስታወቀ። ፓርቲው ይህን አቋሙን የገለጸው፤ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 28 በአዲስ አበባው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በነበረው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ ነው።

የፓርቲውን መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው ዕጩዎች በተገኙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማን፣ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፓርቲው የሚያራምዳቸውን አቋሞች እና አስተሳሰቦች የተመለከቱ ጥያቄዎች ከታዳሚዎች ተነስተዋል። ሶስት መቶ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የከተማይቱ የባለቤትነት እና የልዩ ጥቅምን የተመለከቱ ጉዳዮች እና ራስን በራስ ማስተዳደርን የተመለከቱ ጥያቄዎች ለፓርቲው ዕጩዎች ቀርበዋል።  

ሌሎች ክልሎች በአዲስ አበባ ላይ ያላቸውን ልዩ ጥቅም በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ፤ የኢዜማ መሪ በሰጡት ምላሽ “ለአንድ ብሄር የሚሰጥ ልዩ ጥቅም አይኖርም” ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም አስታውቀዋል። ከአዲስ አበባ መስፋፋት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ደግሞ “አዲስ አበባ መስፋት እስካለባት መስፋት ትችላለች” ብለዋል። ነገር ግን ይህ የከተማዋ መስፋፋት በዙሪያዋ ያሉ ነዋሪዎችን በሚጠቅም እና በማይጎዳ መልኩ መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። 

“አዲስ አበባን በተመለከተ ግልጽ የሆነ አቋም መያዝ አለበት” የሚሉት የፓርቲው መሪ፤ “በምንም አይነት ብልጽግና ተመልሶ አዲስ አበባን ማስተዳደር የለበትም” ሲሉ የውይይቱን ታዳሚዎች አሳስበዋል። የከተማዋን ባለቤትነት በተመለከተ“ ‘አዲስ አበባ የማን ነች?’ የሚለውን ጥያቄ ማጥፋት አለብን። አዲስ አበባ የሁሉም ነዋሪዎቿ ነች፤ አሁን ያሉት ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚመጡትም [ጭምር]” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

ፓርቲውን ወክለው ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ ዮሐንስ መኮንን በበኩላቸው፤ “አዲስ አበባ በማስተዳደር እና በመብት ጥያቄ፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናት” ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ ባሻገር ግን የአዲስ አበባም ሆነ የሌሎች ክልሎች “አስተዳደራዊ መዋቅር መከለስ አለበት” የሚል እምነታቸውን አንጸባርቀዋል።  

ኢዜማ አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ የከተማዋን ከንቲባ ሹመት በተመለከተ ምን እንደሚያደርግ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀርበውለታል። ፓርቲው ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ካቀረባቸው እጩዎች አንዷ የሆኑት ሩሃማ ታፈሰ፤ ፓርቲያቸው ከከተማዋ የምክር ቤት አባላት አወዳድሮ ከንቲባ እንደሚመርጥ አስታውቀዋል።

“በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ከተሞች ህዝቡ በቀጥታ ከንቲባውን እንዲመርጥ እናደርጋለን” ሲሉ ሩሃማ ፓርቲያቸው በዚህ ረገድ ሊያደርግ ያቀደውን ጠቁመዋል። ፕሮፌሰር ብርሃኑም “በእያንዳንዱ የስልጣን እርከን ላይ ያለ የመንግስት ባለስልጣን፤ በህዝብ እንዲመረጥ ነው ፍላጎታችን” ሲሉ የፓርቲያቸውን ዕጩ ሃሳብ አጠናክረዋል። 

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የቤት ችግር የተመለከቱ ጥያቄዎችም በመድረኩ ተነስተዋል። አቶ ዮሐንስ የቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩ የከተማዋን ነዋሪዎች በተመለከተ “እንደ ከዚህ በፊቱ አናፈናቅልም። የቻሉት ራሳቸው እንዲያለሙ፤ ካልሆነ ግን በምናቋቁመው የቤት ባንክ ድጋፍ እንዲገነቡ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል። 

ሌላኛው የፓርቲው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩ አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፤ ኢዜማ በመጪዎቹ አምስት አመታት ከሁለት መቶ ሺህ ያላነሱ ቤቶች ለመገንባት እቅድ እንዳለው አስታውቀዋል። ፓርቲው እነዚህን የቤት ግንባታዎች የሚያሰራው በአገር ውስጥ ተቋራጮች መሆኑንም አመልክተዋል። 

ከመጪው አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ “ኢዜማ ምርጫው ምን ያህል ፍትሃዊ ይሆናል ብሎ ያስባል?” የሚል ጥያቄም ከውይይቱ ተሳታፊዎች ተሰንዝሯል።  “መከራችንን እያየን ያለነው” ሲሉ በምርጫ ቅስቀሳ ችግር ያጋጠማቸውን ችግር ለታዳሚያን ያጋሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ምርጫው አልጋ በአልጋ ይሆናል ብለው ወደ ሂደቱ አለመግባታቸውን አስረድተዋል። ፓርቲያቸው በምርጫው ፍትሃዊ መሆን ላይ ተስፋ እንዳለውም አልሸሸጉም። የፓርቲው የምርጫ ስትራቴጂ እና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከውሰር እድሪስ “ተያይዘን ገደል ስለምንገባ ፍትሃዊ ቢያደርጉት ይሻላቸዋል” ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል ምላሽ ሲሰጡ ተደምጠዋል። 

“ኢዜማ ከብልጽግና ጋር አብሮ ይሰራል ወይ?” ተብለው የተጠየቁት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ “የሀገር ህልውናን፣ አንድነትን በሚያስቀጥሉ ሁኔታዎች ላይ ከማንኛውም አካል ጋር ብልጽግናን ጨምሮ እንሰራለን” ሲሉ መልሰዋል። ፓርቲያቸው ከብልጽግና ጋር ያደረገው “ይፋዊ ቅንጅት” እንደሌለ ያስገነዘቡት የኢዜማ መሪ፤ “ከብልጽግና ጋር መሰረታዊ ልዩነት አለን” ብለዋል። አቶ ክቡር ገናም “ኢዜማ የመንግስት ተቃዋሚ ነው። ተለጣፊ አይደለም” ሲሉ በፓርቲው ላይ የሚነሳበትን ትችት ተከላክለዋል።  

“ኢዜማ የአማራ ህዝብ ሲገደል ዝም ብሏል” በሚል ከተሳታፊ ለቀረበው ጥያቄ፤ “እሱ ዝም ብሎ አሉባልታ ነው። በየትኛውም ቦታ ዜጎች ሲገደሉ ያላወገዝንበት ሁኔታ የለም” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስተባብለዋል። በተጨማሪም የኤርትራ ጦር በሰሜኑ ግጭት ያለውን ተሳትፎ በተመለከተ “ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ከማንኛውም የጎረቤት አገር ጋር የመተባበር መብት አላት” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ፓርቲያቸው የሚያራምደውን አቋም ግልጽ አድርገዋል።  

“በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት ጉዳት ስለደረሰባቸው ዜጎች ያላችሁት ነገር የለም” በሚል ፓርቲው ለቀረበበት ወቀሳ፤ “ሁለት ጊዜ የስራ አስፈጻሚ ልዑካችንን ወደ ክልሉ ልከናል በክልሉ በሚገኙ ከተሞችም ቢሮዎችን ከፍተናል” ሲሉ ምላሽ የሰጡት ከውሰር እድሪስ፤ ፓርቲያቸው ጉዳዩን እየተከታተለው እንደሆነም ተናግረዋል። ከውሰር ቢሮ ከፍተንባቸዋል ያሏቸውን የትግራይ ከተሞች ግን በስም አልጠቀሱም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)