ባልደራስ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ “ዓለም አቀፍ የምርጫ የፍትሃዊነት መርሆዎችን ያላሟላ ነው” አለ

በሃሚድ አወል

የስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የቅድመ ምርጫ ሂደት፤ በተለያዩ ህጎች የተካተቱትን የነጻ፣ የፍትሃዊነት እና የዲሞክራሲያዊ መመዘኛዎች “ዝቅተኛ ደረጃ እንኳ የማያሟላ ነው” ሲል የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ወነጀለ። መጪው ምርጫው ሊካሄድ ሁለት ሳምንት ቢቀረውም፤ ፓርቲው የመራጮች ምዝገባ እንደገና እንዲደረግ ጠይቋል።

ባልደራስ እነዚህን አቋሞቹን ያሳወቀው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የቅድመ ምርጫ ሂደት አስመልክቶ የሰራውን የዳሰሳ ጥናት፤ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 1፤ 2013 ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው። በ25 ገጾች በተዘጋጀው በባልደራስ የዳሰሳ ጥናት፤ የእጩዎች፣ መራጮች እና የፓርቲ አባላት የደህንነት ሁኔታ፤ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የታዩ ሳንካዎች፤ በምርጫ ቦርድ በኩል ተስተውለዋል የተባሉ ችግሮች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጉዳይ፣ የመራጮች መዝገብ ግምገማ እና የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም በስፋት ተዳስሰዋል። 

የፓርቲው የሰብዓዊ መብት እና የህግ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሔኖክ አክሊሉ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ቅድመ ምርጫ ሂደት “ከፍተኛ ችግር የነበረበት ነው” ሲሉ በራስ አምባ ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ በበኩላቸው ለምርጫው “ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ መግባት የገዢው ፓርቲ ችግር እና የምርጫ ቦርድን ድክመት” በምክንያትነት አንስተዋል። 

ባልደራስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የተመለከቱ ጉዳዮችን በዘረዘረበት የጥናቱ ክፍል ላይ፤ በመራጮች ምዝገባ ወቅት ስለተስተዋሉ ችግሮች፣ ስለ ምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት፣ ስለ ምርጫ አስፈጻሚዎች አመላመል ሂደት እንዲሁም የመራጮች መዝገብን ለመመርመር ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ተመልክቷል። ፓርቲው እነዚህን ጉዳዮች የተመለከቱ መረጃዎች ያሰባሰበው “በድፍን አዲስ አበባ” ተዘዋውሮ መሆኑንም አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ለማውጣት ችግሮች ገጥመዋቸው እንደነበር የሚጠቁመው የዳሰሳ ጥናቱ፤ በተለያዩ ምክንያቶች “ብዙ ሰው የምርጫ ካርድ አልወሰደም” ሲል ድምዳሜውን አስፍሯል። የምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት እና የምርጫ ጣቢያዎች ያሉበት ሁኔታ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙብታል። “የምርጫ ካርድ ለመውሰድ የማያስችሉ ሁነቶች መኖራቸውን፤ ቃለ መጠይቅ ካደረግንላቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች ለመረዳት ይቻላል” ብሏል ፓርቲው። 

በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች “ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ዜጎች ካርድ ያወጣሉ” ሲል የወነጀለው ባልደራስ፤ “የምርጫ ካርድ የሚታደለው የዜጎችን ማንነት መሰረት ባደረገ መልኩ ነው” ሲል ከስሷል። ከመራጮች ምዝገባ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በተመለከተ ባካሄደው ጥናት የደረሰበትን ውጤት በሚያዚያ 29፤ 2013 ለምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ቢያሳውቅም፤ ከቦርዱ “ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኘ” ፓርቲው አስታውቋል። 

ባልደራስ በጥናቱ ተቃውሞ ያቀረበበት ሌላው ጉዳይ የምርጫ አስፈጻሚዎች አመላመል ሂደት ነው። “የምርጫ አስፈጻሚዎች አመላመል መሰረታዊ ችግር” ሲል ቅሬታውን የገለጸው ፓርቲው፤ ለዚህም ዋነኛ መንስኤው አስፈጻሚዎቹ የተመለመሉባቸው ተቋማት ናቸው ባይ ነው። ፓርቲው ምርጫ አስፈጻሚዎቹ ተመልምለውባቸዋል ባላቸው በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ፣ በሥራ ፈጠራ ኮሚሽን እና በአዲስ አበባ ሴቶች ሥራ ፈጠራ ማህበር ላይ አመኔታ እንደሌለው በጥናቱ አስታውቋል።

ከምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር በተያያዘ ሌላው ወቀሳ የቀረበበት አካል ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ነው። ባልደራስ “በአንዳንድ የምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ የብልጽግና ካድሬዎች በስራቸው ላይ ጫና ያሳድሩባቸዋል” ሲል በጥናቱ ከስሷል። የፓርቲው የህዝብ ግንኑነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ “አብዛኞቹ የምርጫ አስፈጻሚዎች የብልጽግና ካድሬዎች ናቸው” ሲሉ ወንጅለዋል። 

እርሳቸው ይህን ቢሉም የምርጫ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቱ ግን የመለመላቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ መሆናቸውን ቀደም ሲል በሰጣቸው መግለጫዎች በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ከገዢው አሊያም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ቅሬታ የቀረበባቸው የምርጫ አስፈጻሚዎችን በተመለከተም ጉዳያቸውን መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ መስጠቱንም ማስታወቁ ያታወሳል።   

ተቃዋሚው ባልደራስ ፓርቲ በጥናቱ ካነሳቸው ውስጥ፤ ለተወሰነ ጊዜ ለታዛቢዎች ክፍት የሚደረገው የመራጮች መዝገብ ምርመራ ጉዳይ አንዱ ነው። “እንደ ምርጫ ህጉ መሰረት አብዛኛዎች የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮችን መዝገብ ለማስመርመር ክፍት አይደሉም” ሲል ፓርቲው ወቅሷል። 

የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ “በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነው” የሚል እምነቱን በጥናቱ ያንጸባረቀው ፓርቲው፤ የምርጫ ካርድ ማውጫ ጊዜ እንዲራዘም በድጋሚ ጠይቋል። ባልደራስ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ በተጠናቀቀበት ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የመጪው ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሁለት ሳምንት በቀረው በዚህ ጊዜም፤ ባልደራስ አሁንም ይህን አቋሙን አለመተውን አስታውቋል። የፓርቲው የሰብዓዊ መብት እና የህግ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሔኖክ አክሊሉ፤ “የመራጮች ምዝገባ እንደገና እንዲደረግ ባልደራስ ይጠይቃል” ሲሉ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። 

የመራጮች ምዝገባን፣ የምርጫ ጣቢያዎችን እና የምርጫ አስፈጻሚዎችን በተመለከተ ባልደራስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ ስላቀረበው ውንጀላ የተጠየቀው የመስሪያ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል፤ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ቦርዱ ከዚህ በፊት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበረው የጋራ የውይይት መድረክ ላይ ምላሽ እንደሰጠባቸው አስታውቋል። በፓርቲው የቀረቡ ሌሎች ውንጀላዎችን በተመለከተ ግን ፓርቲው ይፋ ያደረገውን ሙሉ የዳሰሳ ጥናት ሳይመለከት ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። 

የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ከእጩዎች እና መራጮች ደህንነት አኳያ በተገመገመበት የባልደራስ የዳሰሳ ጥናት ክፍል ላይ፤ ምርጫው “የደህንነት ስጋት” ማስከተሉ ተጠቅሷል። ፓርቲው ለዚህ በማሳያነት የጠቀሳቸው በቢሾፍቱ፣ በመተከል እንዲሁም እና በጎንደር መተማ ዩሃንስ የተገደሉ የኢዜማ እና የአብን አባላትን እና የምርጫ ዕጩን ነው። “እነዚህ ግድያዎች የቅድመ ምርጫውን ሂደት ነጻነት እና ፍትሃዊነት አጠያያቂ ያደርገዋል” ሲል ባልደራስ ስጋቱን ገልጿል። 

በእስር ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ሌላው ፓርቲው ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ነው። በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እስር፤ በምርጫው ሂደት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ እጅጉን የጎላ ነው” ብሏል ፓርቲው። የባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራት የፓርቲው አመራሮች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ባልደራስ በተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ወከባ በጥናቱ አንስቷል። “የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ እጩዎች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ ወከባ እንደሚሰነዘር በጥናቱ ለመረዳት ተችሏል” ሲል የሚከስሰው ፓርቲው፤ ለእዚህም ገዢውን የብልጽግና ፓርቲን ተጠያቂ ያደርጋል። “ወከባ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያው” በማህበረሰቡ ላይ ጭምር ይደርሳል የሚለው ባልደራስ፤ “መራጩን ህዝብ ማዋከብ እና ስጋት ውስጥ ማስገባት የብልፅግና ፓርቲ ዋና ተግባር ሁኗል” ሲል ገዢው ፓርቲ ላይ ሌላ ተጨማሪ ውንጀላ አክሏል።  

ባልደራስ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አጋጠሙኝ ያላቸውን ችግሮችንም በዳሰሳ ጥናቱ አካትቷቸዋል። “ገዥው ፓርቲ ካድሬዎቹን በማሰማራት በየድንኳኖቻችን ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ አድርጓል” ሲል ብልጽግናን የሚከስሰው ባልደራስ፤ ከዚህ በተጨማሪ የተከላቸው ባነሮች እንደሚነቀሉ እና እንደሚቀደዱበት ገልጿል። 

በኦሮሚያ ክልል በተደረጉ ሰልፎች “ፓርቲያችንን እንደ ኢትዮጵያ ጠላት፤ በመፈክር ሲፈረጅ እንደነበርና የማሸማቀቅ ተግባር ሲከናወንበት እንደቆየ ማስታወስ ይቻላል” ሲል ባልደራስ ለውንጀላው ማሳያ ነው ያለውን ሁነት ጠቅሷል። “በብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎች ከፍተኛ ጫና እየተደረገብኝ ነው” የሚለው ባልደራስ፤ ይህንኑ ጉዳይ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቅም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል። 

ባልደራስ በዛሬው የዳሰሳ ጥናቱ፤ ፓርቲው በቂ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን አለማግኘቱን በማንሳት ትችቷል። የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ፓርቲዎች ፍትሃዊ ተደራሽነት ሊኖራቸው ይገባ ነበር የሚል እምነቱን የገለጸው ባልደራስ፤ “እንደ ኢ.ቢ.ሲ የመሳሰሉት የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ግን ይሄን ሃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ ባልደራስን በተደጋጋሚ ሲያገሉት ይታያሉ” ሲል ወቅሷል። 

ፓርቲው የብሔራዊ መገናኛ ብዙሃንን ለምርጫ ቅስቀሳ መጠቀም አለመቻሉ ተደራሽቱን እንደገደበ አመልክቷል። ቅስቀሳዎችን ኧእንዲያሰራጭ በተፈቀደለት መገናኛ ብዙሃንም “መረጃዎች እንዳይተላለፉ መከልከል” እንደሚስተዋልም ጠቅሷል። ባልደራስ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋንን በተመለከተ “ችግሩ እንዲቀረፍ ደብዳቤ ብጽፍም ምላሽ አላገኘሁም” ብሏል።

ጉዳዩን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን፤ የአየር ሰዓት ድልድል ኮሚቴ አባል አቶ ደሬሳ ደረሰ፤ በጉዳዩ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መወያየታቸውን በማስታወስ “መስፈርቱ ለሁሉም እኩል ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። አንድ ፓርቲ በብሔራዊ ጣቢያዎች የአየር ሰዓት የሚያገኘው በሚወዳደርበት ክልል መገናኛ ብዙሃን ከሌለው ብቻ መሆኑን ጠቅሰው የባልደራስ የአየር ሰዓት ድልድልም በዚህ መልኩ መካሄዱን ጠቁመዋል።  

“የክልል ፓርቲዎች በክልል ጣቢያዎች ነው የሚቀሰቅሱት። ባልደራስም በአዲስ አበባ ብቻ ስለሚወዳደር በከተማዋ ጣቢያዎች ነው ቅስቀሳ ማድረግ የሚችለው” ሲሉ አቶ ደሬሳ አብራርተዋል። 

ይህ ምላሽ ግን ለፓርቲው የሰብዓዊ መብቶች እና የህግ ዘርፍ ኃላፊ የሚዋጥ አይደለም። እንደ አቶ ሔኖክ እምነት የክልል ፓርቲዎች በክልል ጣቢያዎች እንዲቀሰቅሱ የተደረገው “ባልደራስን ለማግለል ነው”። “በዚህ ጉዳይ ላይ ለምርጫ ቦርድ እና ለመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ደብዳቤ ጽፈናል። ምላሽ ሊሰጡን ግን አልቻሉም” ሲሉ ተቋማቱን ተችተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)