በትግራይ ክልል 131 ጊዜ የእርዳታ ስርጭት መስተጓጎሉን አንድ የተመድ ኃላፊ ይፋ አደረጉ

በትግራይ ክልል 131 ጊዜ የእርዳታ ስርጭት መስተጓጎሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እና አስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ አስታወቁ። የእርዳታ ስርጭቱን በአብዛኛው ያስተጓጎሉት የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ወታደሮች መሆናቸውን ገልጸዋል። የተመድ የእርዳታ አስተባባሪ ይህን የተናገሩት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በጥምረት ባዘጋጁት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ላይ ነው።

በቪዲዮ ኮንፍረንስ አማካኝነት ትላንት ሐሙስ ሰኔ 3 በተካሄደው በዚህ ውይይት፤ በክልሉ የከፋ ረሐብ እንዳይከሰት መከላከል፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት መጠበቅ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግጋት መከበራቸውን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነበር። ውይይቱ በትግራይ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የሰብዓዊ ቀውስ ሳቢያ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ላይ የበረታው ጫና በግልጽ ያሳየ ሆኗል።

የእርዳታ ስርጭት ማስተጓጎልን በተመለከተ የተመድ የእርዳታ አስተባባሪ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ድርጊቱን 54 ጊዜ ሲፈጽሙ፤ የኤርትራ ወታደሮች ደግሞ 50 ጊዜ እርዳታ እንዳይሰራጭ አድርገዋል። የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች በጥምረት አራት ጊዜ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸውንም ገልጸዋል። የአማራ ሚሊሺያ አባላት ለ21 ጊዜ ያህል የእርዳታ ስርጭት እንቅፋት መሆናቸውን ያስረዱት አስተባባሪው፤ በትግራይ ተቃዋሚ ኃይሎች በኩልም አንድ ጊዜ ይህው መፈጸሙን አስረድተዋል።

የድርጊቱን ፈፃሚዎች የኮነኑት ሎውኮክ፤ የእርዳታ ሥርጭቱን ለማጠናከር “ሁሉም ኃይሎች ጠባያቸውን ማሻሻል አለባቸው” ብለዋል። አቅም ያላቸው ሰራተኞች በማሰማራት ስራውን ማጠናከር እንዲሁም ተጨማሪ ገንዘብ መመደብ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ በዘለቀው እና የአሜሪካው ሲ.ኤ.ንኤን. ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ኒማ ኤልጋቢር በመራችው ውይይት፤ የተመድ የእርዳታ አስተባባሪ  በትግራይ ክልል ባለው የሰብዓዊ ሁኔታ ላይም ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸው ትኩረት ካደረጉባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ምላሽ የሰጠበት የጠኔ ጉዳይ ይገኝበታል። 

ማርክ ሎውኮክ ረቡዕ ዕለት ይፋ የሆነ የዳሰሳ ጥናት ጠቅሰው “በአሁኑ ወቅት በትግራይ ጠኔ (famine) አለ” ብለዋል። የእርዳታ አስተባባሪው የጠቀሱት የዳሰሳ ጥናት፤ የሸፈነው በትግራይ እንዲሁም አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች የሚገኙ 83 ወረዳዎችን ነው። የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት፣ ኢጋድ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን የመሳሰሉ ተቋማትን በአጋርነት ያካተተው የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (Integrated Food Security Phase Classification) ስር የተካሄደው ጥናት፤ በ83 ወረዳዎች ውስጥ ከ350,000 በላይ ሰዎች የከፋ የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው አሳይቷል።     

ሎውኮክ “በጥልቀት የተከናወነ” ያሉት ጥናት፤ በትግራይ “የከፋው ቀውስ መፈናቀል፣ የእንቅስቃሴ ገደብ፣ የተገደበ የእርዳታ አቅርቦት፣ የሰብል እና የሐብት ጥፋት እና በቅጡ የማይሰሩ ወይም የጠፉ ገበያዎችን ጨምሮ ግጭት ባስከተላቸው መዘዞች የተከሰተ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። “በጠኔ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በ2011 ሩብ ሚሊዮን ሶማሌያውያን ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ፤ በየትኛውም የዓለም ክፍል በየትኛውም ጊዜ ከታየው ሁሉ የላቀ ነው። ሌሎች ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ከከፋው ሁኔታ አንድ እርምጃ ራቅ ብለው ይገኛሉ” ያሉት ሎውኮክ እነዚህ ሰዎች በትግራይ ክልል አምስት የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙ አስረድተዋል። 

በክልሉ ያለውን አንገብጋቢ ሁኔታ በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት እስካሁን አንድም ግልጽ ውይይት አለማድረጉ ሎውኮክ ከጠቀሷቸው ጉድለቶች አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ አባል የሆነችበት እና አስራ አምስት አባላት ያሉት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ላይ መግለጫ ቢያወጣም ስብሰባዎቹ ሁሉ በዝግ የተደረጉ ናቸው። 

በትግራይ ጉዳይ “ለምክር ቤቱ ሶስት ጊዜ በዝግ ማብራሪያ ሰጥቼያለሁ። በመጪው ማክሰኞ ለተጨማሪ ዝግ ስብሰባ ተጋብዤያለሁ” ያሉት ሎውኮክ፤ ግጭትን በተመለከተ ምክር ቤቱ ከሶስት ዓመታት በፊት ያጸደቀውን የውሳኔ ሀሳብ በመጥቀስ በጉዳዩ ላይ ዝግ ያልሆነ ውይይት አለማድረጉን ተችተዋል። የተመድ የእርዳታ አስተባባሪ በንግግራቸው የጠቀሱት የውሳኔ ሀሳብ፤ ግጭት የከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ከፈጠረ እርሳቸው እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቁ የሚያዝ ነበር።   

ሎውኮክ በተመድ የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ላይ የሰነዘሩትን ወቀሳ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ እና በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ተጋርተውታል። ጄፍሪ ፌልትማን “ይህ በጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ አጀንዳ ላይ መሆን ነበረበት። እስካሁን በጉዳዩ ላይ ግልጽ ውይይት አለመደረጉ አሳፋሪ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።  

የጸጥታ ምክር ቤቱን በውይይቱ መግቢያ ላይ በንባብ ባሰሙት ንግግር የሸነቆጡት ሊንዳ ቶማስ፤ “በትግራይ የተከሰተው አደጋ ሊቀለበስ የሚችል አይደለም። ተመሳሳይ ስህተት ሁለት ጊዜ አንሰራም። ኢትዮጵያ እንድትራብ አንፈቅድም። አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ አለብን” ሲሉ ተደምጠዋል።  

“ምንም እንኳ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በሚያሳዝን ሁኔታ የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ከፊታችን በደቀኑት ጋሬጣ እየታዘብን ያለንውን የሰብዓዊ መብቶች እና የሰብዓዊ ሁኔታ ቀውስ የተመለከተ አንድም ውይይት አላደረገም ወይም እርምጃ አልወሰደም” ያሉት አምባሳደሯ፤ “ምንድነው የምንፈራው? ምንድነው ለመደበቅ የምንሞክረው?” የሚሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል። በሌሎች ቀውሶች ላይ ምክር ቤቱ ግልጽ ስብሰባ ማድረጉን ያስታወሱት አምባሳደሯ፤ የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ በዚሁ ጉዳይ ላይ ውይይት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

“ቀውሱን ለመፍታት ምክር ቤቱ ትርጉም ያለው እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ አሁን ነው” ያሉት ሊንዳ ቶማስ የኢትዮጵያ መንግስት የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ለሚቀርብለት ጥያቄ “ኃላፊነት በተሞላው መንገድ” መልስ እንዲሰጥ፣ ለውጊያው ማብቂያ እንዲያበጅ በክልሉ ጥሰት የፈጸሙትን ተጠያቂ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከባለስልጣናት ጋር የተወያዩት የአውሮፓ ህብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ያስተባበለውን እና ሰላማዊ ሰዎችን ማስራብን እንደ ጦር መሳሪያ የመጠቀም ክስ በድጋሚ አቅርበዋል። “በትግራይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች እና የሰብዓዊ ህግጋት ጥሰቶች ስፋት እና ብርታት አሰቃቂ ነው። ሰላማዊ ሰዎችን በማስራብ እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም የከፋ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰት ነው” ያሉት ሌናርቺች፤ የተኩስ አቁም ተደረሰም አልተደረሰ እርዳታ ለተቸገሩ ሁሉ ያለ ቅድመ ሁኔታ መድረስ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።  

የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን በበኩላቸው የእርዳታ አቅራቢዎች ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንዲፈቀድላቸው፣ ግጭት እንዲቆም እና የኤርትራ ወታደሮች ለቅቀው እንዲወጡ የቀረቡ ጥሪዎች እስካሁን ተቀባይነት አለማግኘታቸውን በንግግራችው አስታውሰዋል። “የተኩስ አቁም ጥሪን ለመቀበል የታየው ዳተኝነት አሳዝኖኛል” ያሉት ዩታ ኡርፒላይነን፤ “ወታደራዊ መፍትሔ እንደማይገኝ ሁላችንም እናውቃለን። ጥያቄያችን እንዲሰማ ጥረታችንን በእጥፍ ማሳደግ ይኖርብናል” ሲሉ ተሳታፊዎቹን አሳሰበዋል። 

“በሺህዎች የሚቆጠር ሕይወት ጠፍቷል። የመላ ኢትዮጵያ ማህበራዊ መስተጋብር ተናግቷል” በማለት ዳፋውን ያብራሩት ዩታ ኡርፒላይነን፤ በትግራይ ያለው ቀውስ በመጪው አገራዊ ምርጫ እና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ጠቁመዋል። “ትግራይ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያላት ድርሻ ስድስት በመቶ ብቻ ነው። ነገር ግን ጉዳቱ ከዚያም ያልፋል። ለኢንቨስትመንት እምነት ወሳኝ ነገር ነው። ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ ሲቀንስ ከኮቪድ-19 በኋላ የሚኖረውን ማገገም አዝጋሚ ያደርገዋል” ብለዋል። 

ከአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን ጋር ኢትዮጵያን ጎብኝተው የነበሩት ዩታ ኡርፒላይነን፤ የኤርትራ ወታደሮች አለመውጣታቸውን፣ 20 ሺህ ኤርትራውያን የደረሱበት እንደማይታወቅ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን ጠቅሰው “በኢትዮጵያ የተከሰተው በዚያው በኢትዮጵያ ተወስኖ አይቀርም” ሲሉ ለአፍሪካ አገራት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ አሁን ላለው ችግር ተጠያቂ በሆኑ አካላት ላይ ጫና ማሳደር እና እርዳታ ለሚፈልጉትም መድረስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

በትላንትናው ስብሰባ ሌላኛው ተናጋሪ የነበሩት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር፤ በትግራይ ክልል የምትኖር የአራት ልጆች እናት እና ነፍሰ ጡር ስለሆነች አንዲት ሴት ጉዳይ አንስተዋል። አጸደ የምትሰኘው ይህቺ የክልሉ ነዋሪ በአምስት ወታደሮች ተገዳ መደፈሯን ለስብሰባው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ሳማንታ “ልብ ሰባሪ” ያሉትን የአጸደን ታሪክ በውይይቱ ያጋሩት በክልሉ ተፈጽመዋል ያሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለማሳየት ነው። ሳማንታ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎች አስገድዶ መድፈር እና የፆታ ጥቃትን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል የሚል ብርቱ ውንጀላ አቅርበዋል። 

በውይይቱ መገባደጃ ማብራሪያ የሰጡት ጄፍሪ ፌልትማን ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ለሚካሔደው የቡድን ሰባት አገራት ጉባኤ በአጀንዳነት ከተያዙት መካከል የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሚገኝበት ተናግረዋል። ፌልትማን “ቀጣዩ አጀንዳችን ምን መሆን እንዳለበት ጥሩ ግንዛቤ አለን። በጋራ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና የእርዳታ ድርጅቶች ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ ግፊት ማሳደር አለብን” በማለት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊከተለው ይገባል ያሉትን መንገድ ጠቁመዋል። “የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ የምናደርገውን ግፊት መቀጠል አለብን” ያሉት ፌልትማን የነፍስ አድን እርዳታ አቅርቦቱ መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።

ልዩ መልዕክተኛው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንገብጋቢ ላሉት የሰብዓዊ እና የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ መፍትሔ ለማፈላለግ ሲባዝን “በመላው ኢትዮጵያ ያለውን ውጥረት እና በቀጣናው ያሉ ፈተናዎችን” መዘንጋት እንደሌለበትም አሳስበዋል። “ኢትዮጵያውያን በመላ ሀገሪቱ የተፈጠሩትን ውጥረቶች ለመፍታት የጋራ መግባባት የሚፈጥር ሁሉን አቀፍ፣ ተዓማኒ፣ አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደት እንዲያበጁ ግፊት ማድረግ አለብን” ብለዋል። በሌሎች አካባቢዎችም “ኹከት፣ ውጥረት እና ችግሮች” መኖራቸውን ጠቅሰው “ፖለቲካዊ እንጂ ወታደራዊ መፍትሔ የለም” ሲሉም መደረግ ያለበትን ጠቁመዋል። 

ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ከአዲስ አበባ እስከ ካይሮ፣ ከሱዳን እስከ ኳታር በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ ላይ ለመምከር ሲጓዙ ስምንት ሳምንታት ያስቆጠሩት ፌልትማን “ስለ ትግራይ፣ ስለ አጠቃላይ ኢትዮጵያ እና ስለ አፍሪካ ቀንድ የሰራነው ትንታኔ በከፍተኛ ደረጃ አንዳቸው ከሌላቸው የተሳሰሩ ናቸው” በማለት የጉዳዩን ውስብስብነት ጠቁመዋል። ፌልትማን ባለፈው ግንቦት መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)