በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን 27 የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂዎች ተገደሉ

በሃሚድ አወል 

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ 27 የጸጥታ ኃይሎች ትናንት ሐሙስ በታጣቂዎች መገደላቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዮት በቀለ እንዳሉት ከተገደሉት የጸጥታ ኃይሎች በተጨማሪ 10 የፌደራል ፖሊስ አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በጸጥታ ኃይሎቹ ላይ ጥቃቱ የተነሰዘረው ከጠዋቱ 1 ሰዓት ገደማ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አብዮት፤ ድርጊቱ የተፈጸመው በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን በማሰስ ላይ ባሉበት ወቅት እንደነበር ይናገራሉ። የጸጥታ ኃይሎቹ በሁለት ዙር ወደ አካባቢው መንቀሳቀሳቸውን የሚያስረዱት ዋና አስተዳዳሪው፤ ጥቃቱ የተሰዘረው በመጀመሪያው ዙር በተጓዙ 47 የፌደራል ፖሊስ እና ሁለት የሚሊሺያ አባላት ላይ ነው ብለዋል። 

ከስምንት አመታት በላይ ያገለገሉ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሁለት ሚሊሺያዎች በበኩላቸው ትናንት ሐሙስ ሰኔ 3፤ አካዩ ቀበሌ በተባለ ቦታ በተፈጸመው ጥቃት 24 የጸረ ሽብር ፖሊስ እና ሁለት የሚሊሺያ አባላት፤ በድምሩ 26 የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ተናግረዋል። ጥቃቱ የተሰነዘረው ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ ጀምሮ መሆኑ የሚገልጹት የሚሊሺያ አባላት፤ በጥቃቱ ስምንት የጸጥታ ኃይሎች ቆስለው ወደ ሻምቡ አጠቃላይ ሆስፒታል “ሪፈር” መባላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

በሁለተኛው ዙር ወደ ቦታው የሄዱት ሚሊሺያዎች ጥቃት ከተፈጸመበት ቦታ ከረፋዱ 3 ሰዓት ገደማ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል። ቦታው ለመደበቅ የሚያስችል ምንም አይነት ጫካ አለመኖሩን ተናግረዋል። የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ አስተዳዳሪም የሚሊሺያዎቹን ገለጻ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል። ቦታው “የታረሰ ማሳ ውስጥ ነው። መንደር ነው። ምንም አይነት ጫካ በአካባቢው የለም” ብለዋል። 

የወረዳው አስተዳዳሪ ለጥቃቱ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።ጥቃት ወደ ተፈጸመበት ቦታ ተሰማርተው የነበሩት የሚሊሺያ አባላት፤ ጥቃት አድራሾቹ የኦነግ ሸኔ አባላት መሆናቸው ላይ ይስማማሉ።  

ታጣቂዎቹ “ስንት እንደሚሆኑ፤ ምን አይነት መሳሪያ እንደያዙ መረጃ ነበረን” የሚሉት አስተዳዳሪው፤ ወረዳው ይህንኑ መረጃ  አሰሳ ለማድረግ ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ ላይ ለነበሩት የጸጥታ ኃይሎች ማሳወቁን ይናገራሉ። ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ 120 የሚሆኑ ታጣቂዎች ይገኙ እንደነበር የደረሳቸውን መረጃ ጠቅሰው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት አቶ አብዮት፤ “19 ብሬል እና 12 ስናይፐርን ጨምሮ ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ታጥቀዋል” ሲሉ የታጣቂዎቹን የትጥቅ አይነቶች ዘርዝረዋል።

ወረዳው የደረሰው መረጃ ላይ ተንተርሶ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለዞን አመራሮች ማሳወቁን እና “አሰሳ ከመደረጉም በፊት ኃይል መጨመር እንዳለበት” አሳስቦ እንደነበር የወረዳው አስተዳዳሪ ያስረዳሉ። ይህንን በተመለከተ ከሆሮ ጉድሩ ዞን ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። 

የጸጥታ ኃይሎቹ ለአሰሳ መንቀሳቀሳቸውን በተመለከተ ታጣቂዎች መረጃ ሳይደርሳቸው እንዳልቀረ አቶ አብዮት በቀለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡ “መረጃውን ለታጣቂዎቹ ማን ነው ያደረሰው?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና አስተዳዳሪው ለጊዜው መረጃ የለኝም ብለዋል። ከጥቃት አድራሾቹ በኩል አንድ ሰው መገደሉን የተናገሩት አቶ አብዮት “ብዙ የተመቱ አሉ” ብለዋል። ይህን ይበሉ እንጂ ስለ ብዛታቸው ሲጠየቁ “በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ ለመገመት እቸገራለሁ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ከጥቃቱ በኋላ ሥጋት ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል። በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ተወልደው ያደጉ እና ስማቸው እንዳጠቀስ የፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ “ከተማው [ጃርቴ] በሰላም ያድራል ብሎ የገመተ አልነበረም” ሲሉ ነበራቸውን ስጋት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አጋርተዋል፡፡

“ነፍሳችን እና ስጋችን ሊላቀቅ ጥቂት ነው የቀረው፡፡ በአካባቢው ያለው ሁኔታ ይረጋጋል ብለን ተስፋ ያደረግነው እነሱ [የፀጥታ ኃይሎች] ስላሉ ነው”

– በሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የሚኖሩ እና በግብርና የሚተዳደሩት የ62 ዓመት ጎልማሳ

በግብርና ሥራ የተሰማሩት እና የዘጠኝ ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ የ40 ዓመት ጎልማሳ “እነሱን [የጸጥታ ኃይሎችን] አምነን ነው በእዚህ ያለነው” ሲሉ የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው መኖር የነዋሪዎች ደህንነት ዋስትና መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡

ሌላ በአካባቢው የሚኖሩ እና በግብርና የሚተዳደሩት የ62 ዓመት ጎልማሳም “ነፍሳችን እና ስጋችን ሊላቀቅ ጥቂት ነው የቀረው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዘጠኝ ቤተሰብ የሚስተዳድሩት እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ግለሰቡ “በአካባቢው ያለው ሁኔታ ይረጋጋል ብለን ተስፋ ያደረግነው እነሱ [የፀጥታ ኃይሎች] ስላሉ ነው” በማለት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)