የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት ፓርቲ፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ሰኔ 14 ካልተካሄደ ከምርጫ ራሴን አገልላለሁ አለ

በሃሚድ አወል

የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ህብረት ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ቀደም ብሎ በተያዘለት ዕለት ሰኔ 14፤ 2013 የማይካሄድ ከሆነ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ራሱን እንደሚያገልል አስታወቀ። ፓርቲው ይህን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔን በተመለከተ ዛሬ እሁድ ሰኔ 6 ባዘጋጀው ውይይት ላይ ነው።

በአዲስ አበባው ኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል በተዘጋጀው በዚህ ውይይት ላይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተዋል። በውይይቱ ላይ በደቡብ ክልል ስር የሚገኙት የቤንች ሸኮ፣ ከፋ እና ዳውሮ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎችም ተሳታፊ ነበሩ።   

የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ህብረት የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ታደሰ ተፈራ “ይህ ሪፈረንደም ከምርጫው በላይ ለህዝቡ ወሳኝ ነው” ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም በውይይቱ ላይ አንጸባርቀዋል። ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔው ለመራዘም በምንያትነት ያቀረበው በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ “የህዝቡን መሰረታዊ እንቅስቃሴ የገደበ የጸጥታ ችግር የለም” ሲሉ የቦርዱን ገለጻ የሚቃረን አስተያየት ሰጥተዋል።  

“ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያ አውጥቶ እና ግብረ ኃይል አደራጅቶ ህዝበ ውሳኔውን አልመራውም” ሲሉን ቦርዱን የወቀሱት የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባል፤ ተፈጠሩ የተባሉ የጸጥታ ችግሮችም ቢሆን በቦርዱ አማካኝነት በጊዜ ሊፈቱ ይገባ ነበር ሲሉ ተችተዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔን ለማራዘም በቦርዱ የተወሰነውን ውሳኔም በስብሰባው ላይ በግልጽ ተቃውመዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ሰኔ 14 ከሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር በአንድ ላይ እንዲካሄድ ቀን ቆርጦለት የነበረውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ወደ ጳጉሜ 1፤ 2013 ማሸጋገሩን ያስታወቀው ባለፈው ሐሙስ ነበር። ቦርዱ ለዚህ ውሳኔው በምክንያትነት የጠቀሰው፤ የህዝበ ውሳኔው በሚደረግባቸው አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ድምጽ የማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች መኖራቸውን ነው።

ሰኔ 14 የድምጽ መስጠት ሂደቱ ከማይከናወንባቸው የደቡብ ክልል አካባቢዎች ውስጥ፤ አምስቱ የሚገኙት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መሆኑን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያመለክታል። ከደቡብ ክልል ወጥተው አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ በመጠባበቅ ላይ ካሉት አካባቢዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የምዕራብ ኦሞ ዞን ሶስት አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እንዳለባቸው ተገልጿል። በቤንች ሸኮ እና በሸካ የምርጫ ክልሎችም ተመሳሳይ ችግር መስተዋሉ ተነግሯል።

ይህ የቦርዱ ገለጻ ያላሳመናቸው የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ህብረት የስራ አስፈጻሚ አባል፤ ፓርቲያቸው ህዝበ ውሳኔው አሁንም ሰኔ 14 መካሄድ አለበት ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል። የቦርዱ ውሳኔ “ተመልሶ የማይታይ ከሆነ በምርጫው ለመሳተፍ እንቸገራለን” ሲሉም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እና ህዝበ ውሳኔው በአንድ ቀን እንዲካሄድ መወሰኑን ፓርቲያቸው ከጅምሩም ሲቃወም እንደነበረ የሚያስታውሱት አቶ ታደሰ፤ ለአካባቢው ነዋሪ ከምርጫው በፊት መቅደም የነበረበት የክልል ምስረታ እንደሆነ ይሟገታሉ። “[ህዝቡ] መጀመሪያ አስተዳደራዊ ክልል ያስፈልገዋል። አስተዳደራዊ ክልል የሌለውን ህዝብ የፖለቲካ ውክልና ስጠኝ ማለት ትክክል አይደለም” ሲሉም አክለዋል። 

የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ህብረት ፓርቲ ከትላንት በስቲያ አርብ ባወጣው መግለጫ ተመሳሳይ ይዘት ያለውን አቋም አንጸባርቋል። “የህዝበ ውሳኔ ጉዳይ ከብሔራዊ ምርጫ ጋር በፍጹም መገናኘት እንደሌለበት የተቃውሞ ሀሳባችንን ስናሰማ ቆይተናል” ያለው ፓርቲው፤ “ሁለቱ መርሃ ግብሮች በአንድ ላይ ሲሆኑ መራጩ ማህበረሰብ ላይ ሊያስክትል የሚችለውን ጫና ለመቀነስ” ሲባል ህዝበ ውሳኔው ከሰኔ 14፤ 2013 በፊት መደረግ እንዳለበት አሳስቧል።    

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ማቴዎስ ሁሴንም፤ ህዝበ ውሳኔው እና ሀገራዊ ምርጫው በተመሳሳይ ቀን አንዲካሄድ መወሰኑ “አግባብ አልነበረም” ሲሉ የሌላኛውን ተቃዋሚ ፓርቲ ሀሳብ ደግፈዋል። በዛሬው ውይይት ተሳታፊ የነበሩት የቤንች ሸኮ፣ ከፋ እና ዳውሮ ዞኖች አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው የህዝበ ውሳኔው መራዘም በሚያስተዳድሩት አካባቢ ላይ ውጥረት መፍጠሩን አስረድተዋል።

 የአካባቢው የክልልነት ጥያቄ “30 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው” የሚሉት የካፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይ ተሰማ፤ “ህዝቡ ሪፈረንደሙን እያየው ያለው ልጅ ወልዶ እንደመሳም ነው” ሲሉ ህዝበ ውሳኔው ለአካባቢው ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ ገልጸዋል። የህዝበ ውሳኔው መራዘም “ለእኛም ፈተና ነው። ዱብ እዳ ነው የሆነብን” ያሉት አቶ በላይ፤ ይህንን ተከትሎ “የማንጠብቃቸው ነገሮች ሊገጥሙን ይችላሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“መቆጣጠር የማንችልበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ህዝበ ውሳኔ ሰኔ 14 ይካሄድ” ሲሉ የካፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ተማጽኗቸውን ለምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች አቅርበዋል። የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማንም በውይይቱ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።   

“አሁን ያሉ ነገሮች ኢ-ተገማች ናቸው” ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ፤ የህዝበ ውሳኔውን መራዘም ተከትሎ በአካባቢው “ስጋት አለ” ብለዋል። በተጨማሪም በሚያስተዳድሩት ዞን የጸጥታ ችግር አለበት በሚባለው የሸኮ ምርጫ ክልል፤ ከ95 በመቶ ህዝብ በላይ መመዝገቡን በማንሳት በጸጥታ ችግር ምክንያት ህዝበ ውሳኔውን ማራዘም አይገባም ሲሉ አሳስበዋል።  

የዳውሮ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ በዛብህ በበኩላቸው፤ ህዝበ ውሳኔው መራዘሙ “ህዝቡ ላይ ከፍተኛ ብዥታ ነው የፈጠረው” ሲሉ ተናግረዋል። በሚያስተዳድሩት ዞን በተካሄዱ የምርጫ ቅስቀሳዎች “ህዝበ ውሳኔው መራዘሙን የሚቃወሙ መልዕክቶች” መተላለፋቸውንም የጠቀሱት አቲ ተክሌ፤ “ይህ ተገማች ያልሆኑ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል” ሲሉ የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳዳሪን ሃሳብ አጠናክረዋል። 

የዛሬውን ውይይት የመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ህዝበ ውሳኔው የተራዘመው በጸጥታ ምክንያት ችግር ያጋጠማቸው አካባቢዎች ብዙ ስለሆኑ ሳይሆን፤ ህዝበ ውሳኔው ሁሉን ያሳተፈ እንዲሆን ስለተፈለገ ነው ሲሉ  አስረድተዋል። “ቦርዱ ተነጋግሮ የሚያሻሽለው ነገር ካለ በአፋጣኝ ውሳኔ እንሰጣለን” ሲሉም ለተሰብሳቢዎቹ ቃል ገብተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)