አምስት ፓርቲዎች፤ ምርጫው “መሰረታዊ መመዘኛዎችን የማያሟላ ነው” አሉ

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ “መሰረታዊ መመዘኛዎችን የማያሟላ ነው” ሲሉ አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዛሬ እሁድ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ። ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው “አስቻይ ሁኔታዎች በሌሉበት የሚካሄድ ምርጫ፤ ሀገር በጉጉት ወደምትጠብቀው ስርዓት አያሸጋግርም” ሲሉ በምርጫው ላይ ያላቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል። 

በአዲስ አበባው ራስ አምባ ሆቴል አቋማቸውን በጋራ ያሳወቁት አምስት ፓርቲዎች፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ(ባልደራስ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ እናት ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ናቸው። የቅድመ ምርጫ ሂደቱን “በብዙ ችግሮች እና ውጣ ውረዶች የተሞላ” ሲሉ የገለጹት ፓርቲዎቹ፤ በዚህ ወቅት በፓርቲዎች ላይም ሆነ በአጠቃላይ አካሄዱ ላይ የተስተዋሉ ያሏቸውን ተግዳሮቶች በመግለጫቸው ላይ ዘርዝረዋል።

አምስቱ ፓርቲዎች በምርጫው በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥማቸውም ራሳቸውን ከምርጫው እንደማይገልሉ ተናግረዋል። 

“የምርጫውን ውጤት ምንም ይሁን ምን ትቀበላላችሁን?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲዎች “ብያኔያቸውን” የሚሰጡት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን እና ቆጠራውን ከተመለከቱ በኋላ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “ውጤት መቀበል አለመቀበል በአጠቃላይ ሂደት ድምር ግምገማ ላይ ተመስርተን የምናደርገው ነው የሚሆነው” ሲሉም ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)