የዛሬ ሳምንት ሰኞ ለሚካሄደው ምርጫ የሚያገለግሉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ከዛሬ ሰኞ ሰኔ 7 አመሻሽ ጀምሮ ወደ ምርጫ ክልሎች ማሰራጨት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ሰኔ 14 በሚካሄደው ምርጫ የድምጽ አሰጣጡ የሚካሄደው በ44,372 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሆነም ገልጿል።
የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ዛሬ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ቦርዱ እስካሁን ሲያጓጉዝ የቆየው ለምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና የሚውሉ ሰነዶችን እንዲሁም ከፍተኛ ጥንቃቄ የማይጠይቁ እንደ ማሸጊያ ሳጥን አይነቶቹን ቁሳቁሶችን ነው። ኃላፊዋ በመግለጫቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ወደ ምርጫ ክልሎች ማጓጓዝ እስካሁን የቆየበትን ምክንያትም ለጋዜጠኞች አብራርተዋል።
“የድምጽ መስጫ ወረቀት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ (sensitive material) ስለሆነ፤ ቀኑ [ለምርጫ] በተጠጋ ቁጥር ነው ማድረስ ያለብን። ቀድመን አድርሰን በተለያዩ ቦታዎች ላይ የጥበቃ፣ የማስቀመጥ የመሳሰሉትን አደጋዎች ለመቀነስ ነው” ሲሉ ምክንያቱን አስረድተዋል።
የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ከዚህ በተጨማሪ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሂደትን በተመለከተ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ትላንት እሁድ ሰኔ 6 በጋራ ስላወጡት የአቋም መግለጫ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል። አምስቱ ፓርቲዎች ምርጫው “መሰረታዊ መመዘኛዎችን የማያሟላ ነው” ሲሉ የሰጡት መግለጫ “ኃላፊነት የማይሰማው ነው” ብለዋል ሶልያና። ምርጫው ሊካሄድ አንድ ሳምንት በቀረው በዚህ ጊዜ ፓርቲዎች እንደዚህ አይነት መግለጫ ማውጣታቸው “ከታለመለት ዓላማ ተቃራኒ የሆነ ውጤት የሚያመጣ ነው” ሲሉም አክለዋል።
“በተለይ ራሳቸው በሚሳተፉበት፣ ዕጩዎቻቸው ባሉበት እና የድምጽ መስጫ ቀን አንድ ሳምንት በቀረው ጊዜ ውስጥ የምርጫ ሂደትን አስመልክቶ ድምዳሜ ላይ የሚደርስ (conclusive) መግለጫዎችን መስጠት ኃላፊነት የሚሰማው ተግባር አይደለም” ሲሉ የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ይህ ማለት ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደቱ ላይ ያጋጠሟቸውን ችግሮች መናገር የለባቸውም ማለት አይደለም” ያሉት ሶልያና፤ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እና በሌሎችም እንቅስቃሴዎቻቸው የሚጋጥሟቸውን ተግዳሮቶችን የተመለከቱ ማብራሪያዎች የመስጠት መብት እንዳላቸው ጠቁመዋል። ነገር ግን የድምጽ አሰጣጡ ገና ባልተከናወነበት ሁኔታ ምርጫው “መመዘኛዎችን ያላሟላ ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ፤ ግምገማውን “ሙሉ አያደርገውም” ብለዋል።
ባልደራስ፣ አብን፣ እናት ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ እና መኢአድ ትላንት እሁድ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ “በብዙ ችግሮች እና ውጣ ውረዶች የተሞላ” እንደሆነ ገልጸው፤ በሂደቱ የታዩ ጉድለቶች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ፓርቲዎቹ “አስቻይ ሁኔታዎች በሌሉበት የሚካሄድ ምርጫ፤ ሀገር በጉጉት ወደምትጠብቀው ስርዓት አያሸጋግርም” ሲሉም ምርጫው ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ እንደማይሆን ጠቁመዋል። (በተስፋለም ወልደየስ- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)