እነ ጃዋር መሐመድ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ

በሃሚድ አወል 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ 24 ተከሳሾች “ለማህበረሰቡም ለተከሳሾችም ደህንነት” ሲባል በዛሬው ዕለት ችሎት ፊት እንዳይቀርቡ ማድረጉን ገለጸ። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በአካል እንዳይገኙ ያደረገው ሰኔ 14 ከሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል።  

ባለፉት ቀናት የምርጫ ቅስቀሳ ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፤ ተከሳሾች ወደ ፍርድ ቤት ሲመጡ ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ብሏል። “ተከሳሾችን በከፍተኛ ጥበቃ ወደ ፍርድ ቤት እንዲመጡ ማድረግ ለማረሚያ ቤቱ አስቸጋሪ ነው” ሲልም ለተከሳሽ ጠበቆች አስረድቷል። 

የእነ ጃዋር መሐመድ ጠበቆች በበኩላቸው “ደንበኞቻችን ባልቀረቡበት ሁኔታ እኛ በችሎት መሰየም አንችልም” ሲሉ የዛሬው ችሎት እንዳይሰየም ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል። “ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የተደረገው በበቂ ምክንያት ነው” ያለው ፍርድ ቤቱ፤ “የተከሳሾች አለመቅረብ እናንተን በችሎቱ ከመሰየም አያግዳችሁም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። 

የልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ- ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ለዛሬ ቀጥሮ የነበረው፤ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች አሉባቸው የተባለውን የደህንነት ስጋቶች በተመለከተ የተከሳሽ ጠበቆችን ምላሽ ለማድመጥ ነው። የእነ ጃዋር ጠበቆች ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ማመልከቻ እንደደረሳቸው ነገር ግን መልስ ለመስጠት እንደማይችሉ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።     

“ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ማመልከቻ ላይ መልስ ሰጥተን፤ ለተከሳሾች ሰጥተናቸዋል። ያዘጋጀነው መልስ ያለው ማረሚያ ቤት ነው። እነሱ ይዘው ይመጣሉ ብለን ነበር። [እኛ] መልስ አልያዝንም” ሲሉ በተለዋጭ ቀጠሮ መልስ ይዘው እንዲቀርቡ ይፈቀድላቸው ዘንድ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።  

የተከሳሽ ጠበቆች ያነሱት ጥያቄ ላይ በፍርድ ቤቱ አስተያየት የተጠየቀው ዐቃቤ ህግ በበኩሉ፤ “በተለዋጭ ቀጠሮ መልስ ይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ይሰጥልን” ሲል ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል። በዚህም መሰረት ዐቃቤ ህግ የምስክሮቹን የደህንነት ስጋቶች በተመለከተ ባቀረበው ዝርዝር ላይ የተከሳሽ ጠበቆችን መልስ ለመስማት ለሰኔ 21፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዛሬው ችሎት የተከሳሽ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ተጨማሪ አቤቱታ አቅርበዋል። ጠበቆቹ የችሎት ዘገባዎችን እና ሪፖርቶችን ለአውሮፓ ህብረት የሚያቀርቡ ግለሰብ እንዳሉ አመልክተው በእርሳቸው ላይ ያላቸውን ቅሬታ አሰምተዋል።  

“ግለሰቡ ደንበኞቻችንን በተመለከተ የሚያስተላልፉት ነገር የተዛባ እና ቀናነት የሌለው ስለሆነ፣ ከደንበኞቻችን አኳያ ሲታይ የሚያቀርቡት ዘገባ የተዛባ እና የደንበኞቻችንን ስም የሚጠፋ ስለሆነ፤ መሰል ዘገባ እና ሪፖርት እንዳይሰሩ ትዕዛዝ ይሰጥልን” ሲሉ የተከሳሽ ጠበቆች ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። “ከሚዲያ ውጭ በግለሰብ የሚቀርቡ ሪፖርቶች፤ የደንበኞቻችንን ፈቃድ ሳያገኙ መዘገባቸው የእነሱን [የተከሳሾችን] ስም ያጎድፋል” ሲሉም አክለዋል። 

ጠበቆች ያቀረቡትን አቤቱታ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ “ገና ለገና አንዱን ወገን ደግፎ ሌላውን ተቃውሞ ይዘግባል ብለን የምናስቀምጠው ገደብ የለም። አቤቱታው ትዕዛዝ የሚሰጥበት አይደለም። ችሎቱ ፍቃድ ሰጪም ከልካይም አይደለም” ሲል የተከሳሽ ጠበቆች አቤቱታ ውድቅ አድርጎታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ፤ ጠበቆች ስላቀረቡት አቤቱታ በተጠቀሰው ክፍል ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበታል]