በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራን በመግደል በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባለው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በሞት እንዲቀጣ ተጠየቀ። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዛሬ አርብ ጥያቄውን ያቀረበው የአስር አለቃ መሳፍንትን የክስ ሂደት ለሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።
ዐቃቤ ህግ ዛሬ ሰኔ 11 ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ባለ ሶስት ገጽ የቅጣት አስተያየት፤ በተከሳሹ ላይ ሶስት የቅጣት ማክበጃዎችን ጠቅሷል። ተከሳሹ ወንጀሉን የፈጸመው የተጣለበትን ኃላፊነት ያለአግባብ በመገልገል መሆኑ፣ ወንጀል ለመፈጸም በተደረገ ስምምነት መሰረት መሆኑ እና ተከሳሽ ወንጀሉን ያደረገው በስራው ሁኔታ ምክንያት ልዩ ጥበቃ በሚሻውና በበላይ አለቃው ላይ መሆኑን በቅጣት ማክበጃነት ዘርዝሯል።
ጉዳዩን የሚመለከተው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጸረ-ሽብርና የሕገ መንግስት ጉዳዮች ችሎት፤ እነዚህን ሶስት የቅጣት ማክበጃዎች ተቀብሎ በተከሳሽ ላይ የሞት ቅጣት ፍርድ እንዲያስተላልፍ ዐቃቤ ህግ ጠይቋል። ተከሳሽ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የለበትም ያሉት የተከሳሽ ጠበቆች፤ ዐቃቤ ህግ “አንድም [የወንጀል] ሪከርድ ሳያቀርብ የሞት ፍርድ መጠየቁ ከህጉ ያፈነገጠ ነው” ሲሉ የአቃቤ ህግን የቅጣት አስተያየት ተቃውመዋል።
ጠበቆቹ ከዚህ በተጨማሪም “የወንጀል ድርጊቱ በስምምነት የተፈጸመ ነው” በሚል በዐቃቤ ህግ የቀረበውን የቅጣት ማክበጃ ላይም መከራከሪያ አቅርበዋል። ከአስር አለቃ መሳፍንት ሁለት ጠበቆች ውስጥ አንደኛው፤ “አብረውት ስምምነት ፈጽመዋል የተባሉት ተከሳሾች ክሳቸው ተነስቷል። ተከሳሽ በዚህ ጉዳይ ጥፋተኛ የተባለው ብቻውን ነው። ማንም አብሮት ጥፋተኛ ባልተባለበት ሁኔታ ማክበጃ ሆኖ ሊያዝ አይገባም” ሲሉ ተሟግተዋል።
ዐቃቤ ህግ “የወንጀል ድርጊቱ በስምምነት የተፈጸመ ነው ማለቱ፤ ተከሳሽ ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ድንጋጌ የሚያቃውስ ነው” ሲሉም ተከራክረዋል። በወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት “ፍርድ ቤቶች የሚወስኑት ውሳኔ ተገማች እና አስተማሪ ነው” ያሉት የተከሳሽ ጠበቆች፤ “ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን የሞት ቅጣት ውድቅ አድርጎ፤ ተከሳሹን የሚያርም፣ ሌሎች ሰዎችንም የሚያስተምር እና የወንጀል ህጉን ዓላማ የሚያሳካ ቅጣት” በተከሳሽ ላይ እንዲወስን ጠይቀዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች “የተከሳሽን መልካም ባህሪ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪነት፣ የተከሳሽን የጤና ሁኔታ እና በመከላከያ ሰራዊት አባልነት ለስድስት ዓመታት ማገልገሉን” በቅጣት ማቅለያነት አቅርበዋል። ለእነዚህም ማስረጃ ናቸው ያሏቸውን ሰነዶች አያይዘዋል።
ከቅጣት ማቅለያ ጋር በቀረበው የጽሁፍ ማስረጃ ላይ ግን ዐቃቤ ህግ ጥያቄ አንስቷል። የጽሁፍ ማስረጃው “ትክክለኛ እና አግባብነት ላይ ማጣራት ስለሚያስፈልግ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠን” ሲል ዐቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የግራ ቀኙን አስተያየት ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ዐቃቤ ህግ የተከሳሽ ጠበቆች ባቀረቡት የቅጣት አስተያየት ላይ የሚያደርገውን ማጣራት ጨርሶ ከቀጠሮ ቀን በፊት ለፍርድ ቤቱ እንዲያስገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ በአስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 21፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)