በተስፋለም ወልደየስ
በየሳምንቱ ቅዳሜ ለንባብ የምትበቃው “ፍትሕ” መጽሔት የዛሬ ዕትም ለገበያ እንዳይቀርብ በመንግስት ታግዶ መዋሉን አዘጋጆቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። መጽሔቷ ታግዳ የነበረችው ለአንባቢያን ከመሰራጨቷ በፊት ከማተሚያ ቤት ሳትወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመጽሔቷ አዘጋጆች እና የህትመት ክትትል ባለሙያዎች የመጽሔቷን መታገድ የሰሙት ዛሬ ረፋድ ላይ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ኢትዮ ከለር አታሚዎች” የተሰኘው ማተሚያ ቤት ባለሙያዎች፤ ቅጽር ግቢያቸው በአራት የፖሊስ አባላት እየተጠበቀ እንደሆነ ከነገሯቸው በኋላ የመጽሔቱን ስርጭት የሚያከናውኑት ግለሰቦች ወደ ቦታው ለመሄድ የነበራቸውን እቅድ መሰረዛቸውንም አስረድተዋል።
ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ሩፋኤል አካባቢ ወደሚገኘው ማተሚያ ቤት ያቀናው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ሶስት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የደንብ ልብስ የለበሱ የፖሊስ አባላትን በቅጽር ግቢው በር ላይ ተመልክቷል። የማተሚያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጸጋዬ አላምረው ከሶስት ፖሊሶች ጋር በመሆን ከግቢው ወጥተው በአካባቢው ካሉ ወጣቶች ጋር ተነጋግረው ተመልሰው ሲገቡም ለማየት ችሏል።
ጉዳዩን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ፤ ዛሬ ስለተከሰተው ሁኔታ የትኛውም የመንግስትም ሆነ የጸጥታ አካል አስቀድሞ እንዳላነጋገራቸው ገልጸዋል። ጉዳዩን የሰሙትም በስልክ እንደሆነ ጠቁመዋል።
“ማንም ያነጋገረን፣ የመጣ ህጋዊ ሰው የለም። ከማገዳቸው በፊት ‘ከምርጫ ጋር ግንኙነት ያለው ነገር አለው ወይ? ብለው ቢጠይቁን ማብራሪያ እንሰጣቸው ነበር። እኛን ሳያነጋግሩ ፖሊስ ልከው ማተሚያ ቤቱን ከብበው ነው እንዳይወጡ ያደረጉት” ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
በልህቀት የህትመት፣ ብሮድካስት እና ኮሚዩኒኬሽን ስራዎች ድርጅት አማካኝነት የምታተመው ፍትሕ መጽሔት፤ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በማጠነጥን ላለፉት ሁለት ዓመት ከሰባት ወራት በህትመት ላይ የቆየች ናት። በዛሬው ዕለት ለገበያ ሊቀርብ የነበረው ዕትሟ የሽፋን ገጽ የአዲስ አበባ ጉዳይን የሚመለከት ነበር።
“ለአዲስ አበባ አይሆኑም” በሚል በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ የሰፈረ ርዕስ የተሰጠው ይሄው የመጽሔት ሽፋን፤ በተመስገን ደሳለኝ የተጻፈን ጹሁፍ የሚያስተዋውቅ ነው። ለጹሁፉ የመረጠውን ርዕስ የተዋሰው ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ሲዘዋወር ከነበረ ሃሳብ መሆኑንም የጠቆመው ተመስገን፤ አንባቢዎቹ “አዲስ አበባን ማን ይታደጋት?” የሚለውን ጥያቄ እያሰላሰሉ ጽሁፉን ያነብቡ ዘንድ ይጋብዛል።
ከነገ በስቲያ ሰኞ ከሚካሄደው ምርጫ አንድ ቀን አስቀድሞ ለንባብ ይበቃ የነበረው “ፍትሕ” መጽሔት፤ በውስጡ የያዘው ሙሉ ይዘቱ ምን እንደው ሳይታወቅ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ዘንድ ከትላንት ምሽት ጀምሮ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጹሁፉ ከምርጫው በፊት የግድ መነበብ ያለበት እንደሆነ ምክር ሲሰጡ፤ ሌሎች ደግሞ መጽሔቱ ያስተዋወቀው ርዕሰ ጉዳይ በጽሞና ጊዜ መነሳቱ አግባብ ነው? ሲሉ ጠይቀዋል።
የ“ኢትዮ ከለር አታሚዎች” ቅጽር ግቢን ለሰዓታት ሲጠብቁ የቆዩት የፖሊስ አባላት፤ ስለ መጽሔቱ መረጃ የደረሳቸው ከትላንት ምሽት አራት ሰዓት ጀምሮ እንደው ሲናገሩ መደመጣቸውን የመጽሔቷ አዘጋጆች ተናግረዋል። የመጽሔቱ ስርጭት ከመሸ በኋላ ይከናወናል በሚል ስጋትም አካባቢውን ለሊቱን ሙሉ ሲጠብቁ ማደራቸውን መናገራቸውንም ጠቅሰዋል።
ፖሊሶቹ የመጽሔቷን ኮፒ “የበላይ አካላት” ላሏቸው ግለሰቦች መውሰዳቸውን የሚናገሩት አዘጋጆቹ፤ ከግለሰቦቹ ምላሽ ካገኙ በኋላ መጽሔቱ መሰራጨት እንደሚችል ለማተሚያ ቤቱ ሰዎች መናገራቸውን አብራርተዋል። “ ፖሊሶቹ ‘የበላይ አካል አንብቦ ቢወጣ ችግር አይፈጥርም’ ብለዋል” ሲሉ የመጽሔቷ አንድ አዘጋጅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ከዛሬ ንጋት ጀምሮ እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የቆየው የ“ፍትሕ” መጽሔት ስርጭት እግድ መቆሙን የተረዱት አዘጋጆች እና የስርጭት ባለሙያዎች፤ የመጽሔቷን 137ኛ ዕትም በነገው ዕለት ለንባብ እንደሚያበቁ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት የ“ፍትሕ” መጽሔትን እንዳይሰራጩ አድርገዋል መባሉን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የከተማይቱ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ “ስለ ጉዳዩ መረጃ የለኝም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “እንዴት ተከለከለ፣ እንዴት ተፈቀደ የሚለውን አላውቀውም” ሲሉ ኮማንደር ፋሲካ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በ“ፍትሕ” መጽሔት ላይ ተወሰደ የተባለው እግድ ለአዘጋጆቹ እንግዳ አይደለም። በሐምሌ 2004 ዓ.ም ለንባብ ልትበቃ የነበረችው የ“ፍትሕ” ጋዜጣም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ እንደገጠማት የሚታወስ ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት እና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ቃለ ምልልስን አስተናግዳ የነበረችው የያኔዋ የ“ፍትሕ” ጋዜጣ፤ ከመታገድም በዘለለ የመቃጠል እርምጃ እንደተወሰደባት ጋዜጠኛ ተመስገን ያስታውሳል።
“ከዚህ በፊትም ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት 30 ሺህ አቃጥሎብናል። እነርሱም በተመሳሳይ ሁኔታ ማተሚያ ቤቱን ከብበው አድረው ጋዜጣው እንዳይታተም አድርገው ነበር” ይላል ተመስገን። ከእገዳው በኋላ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በተደረገ ውይይት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ሞት የተመለከተውን ዜና እና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ቃለ ምልልስ በማስቀረት ሌሎቹን ይዘቶች ማተም እንደሚችሉ እንደተነገራቸውም ይገልጻል።
መንግስት ያቀረበውን ይህን ጥያቄ አለመቀበላቸውን የሚያስረዳው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ በዚህም ምክንያት ጋዜጣው ተሰብስቦ እንዲቃጠል ተደርጓል ይላል። የ1985 የኢትዮጵያ የፕሬስ ሕግም ሆነ በ2002 የወጣው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ፤ በህትመት ውጤቶች ላይ የሚወሰዱ የእገዳ እርምጃዎችን በተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌዎችን አካትተዋል።
ማሻሻያዎች ከታከሉበት በኋላ ቀደምት ህጎችን ተክቶ በዚህ ዓመት የጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅም “የእገዳ እርምጃዎችን ስለመውሰድና እግድ ስለመጣል” የሚደነግግ አንቀጽ በውስጡ ይዟል። በአዋጁ መሰረት አንድ በየጊዜው የሚወጣ ህትመት እንዳይሰራጭ የሚደረገው “በብሔራዊ ደኅንነት ላይ፤ ከስርጭት በኋላ በማስቀጣት ሊቀለበስ የማይችል፤ ግልጽና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል” ሲሆን ነው።
በአዋጁ መሰረት አንድ በየጊዜው የሚወጣ ህትመት እንዳይሰራጭ የሚደረገው “በብሔራዊ ደኅንነት ላይ፤ ከስርጭት በኋላ በማስቀጣት ሊቀለበስ የማይችል፤ ግልጽና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል” ሲሆን ነው።
የፌዴራል ወይም የክልል ዐቃቤ ሕግ እንዲህ አይነት ህትመት ሊሰራጭ መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ሲኖረው፤ የህትመት ውጤቱ እንዳይሰራጭ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንዲያዝ ማመልከት እንደሚችል በአዋጁ ላይ ተደነግጓል። ከነገሩ አጣዳፊነት የተነሳ ዐቃቤ ሕግ ጉዳቱን ለመከላከል የፍርድ ቤት የማገጃ ት ዕዛዝ በፍጥነት ማግኘት ባልቻለ ጊዜ፤ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ውሳኔ በየጊዜው የሚወጣ ህትመት ስርጭት እንዲታገድ ትእዛዝ ሊሰጥ እንደሚችልም በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።
ሆኖም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ይህንን ውሳኔ በሰጠ በ48 ሰዓት ውስጥ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ማስታወቅ እንዳለበት አዋጁ ያዝዛል። እግዱ በ48 ሰዓት ለፍርድ ቤት ካልቀረበም እንደተነሳ እንደሚቆጠርም አዋጁ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)