ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ በድጋሚ እንደማይከናወን ተገለጸ

በሃሚድ አወል 

በመጪው ጷጉሜ ወር መጀመሪያ ለሚካሄደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ በድጋሚ እንደማይከናወን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ መራጮች ለተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤት ድምጽ በሚሰጡበት ጊዜ የሚጠቀሙበት የምዝገባ ካርድ፤ ጷጉሜ 1 ለሚከናወነው ህዝበ ውሳኔም የሚያገለግል መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።   

የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ በሌሎች ቦታዎች ድምጽ ከተሰጠ በኋላ የምርጫ ካርዶች የሚወሰዱ ሲሆን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች ግን ይህ አካሄድ ተፈጻሚነት አይኖረውም። “ምርጫው እና ህዝበ ውሳኔው በአንድ ቀን ይካሄዳል ብለን፤ የመራጮች ምዝገባ ያከናወነው በአንድ ላይ ነው” ያሉት ሶልያና፤ ሆኖም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ ባለመከናወኑ ህዝበ ውሳኔው ወደ ጷጉሜ 1 መዛወሩን አስታውሰዋል። 

የመራጮች ምዝገባ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ መራጮች ከነገ በስቲያ ሰኔ 14 በሚካሄደው ምርጫ ድምጽ ከሰጡ በኋላ፤ የመራጮች ካርዶቻቸው በምርጫ አስፈጻሚዎች ተፈርሞባቸውና ማህተም ተደርጎባቸው እንደሚመለሱላቸው ሶልያና አስረድተዋል። በዚህም መሰረት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ እና ሰኔ 14 ድምጽ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ያሉ መራጮች ለምርጫው ድምጽ በሰጡበት ካርድ ለህዝበ ውሳኔውም ድምጽ የሚሰጡ ይሆናል። 

የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ዛሬ ሰኔ 12 በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ፤ ቦርዱ ባለፉት ቀናት ሲያከናውነው የነበረው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ስርጭት ያለበትን ደረጃም አብራርተዋል። ወደ ክልሎች የሚደረገው ስርጭት ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን የተናገሩት ሶልያና፤ በአዲስ አበባ ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የተጀመረው ስርጭትም በነገው ዕለት ይጠናቀቃል ብለዋል።  

በዛሬው መግለጫ፤ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጭ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ በተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮች ጉዳይም ተነስቷል። ቦርዱ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮችን አስመልክቶ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት፤ መራጮቹ በምርጫ ጣቢያዎች በመቅረብ እንደ አዲስ ምዝገባ እያከናወኑ እንደሚመርጡ አብራርተዋል።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ አበባ ሁለት፤ በድሬዳዋ ደግሞ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎች ከዕውቅናው ውጭ መከፈታቸውን አስታውቆ ነበር። ከሁለቱ ከተማዎች ውጭ ከቦርዱ እውቅና ውጭ የምርጫ ጣቢያዎች በብዛት ተከፍተው የተገኙት በደቡብ ክልል ነው። በክልሉ 71 የምርጫ ጣቢያዎች በዚህ መልክ ተከፍተው ማግኘቱን ቦርዱ መግለጹ ይታወሳል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)