በሃሚድ አወል
በነገው ዕለት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ አምስት የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በምርጫ ክልሎቹ ድምጽ እንዳይሰጥ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የድምጽ መስጫ ወረቀቶች “ተነካክቶ መገኘት” እና የምርጫ አስፈጻሚዎች እጥረት እንደሚገኝበት ቦርዱ ገልጿል።
ምርጫ ከማይካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ ሶስቱ የሚገኙት በአማራ ክልል ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል መሆኑን የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ዛሬ እሁድ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። በአማራ ክልል ምርጫ የማይካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች ደምቢያ፣ ተሁልደሬ 1 እና ተሁልደሬ 2 ሲሆኑ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ግንደ በረት እና ነገሌ የምርጫ ክልሎች ናቸው።

በደምቢያ፣ ተሁልደሬ 1 እና ተሁልደሬ 2 የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁሶች እና ሰነዶች የሚታሸጉባቸው ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው መገኘታቸውን የገለጹት ሶልያና፤ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችም “ተነካክተው ተገኝተዋል” ብለዋል። ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ በደምቢያ የምርጫ ክልል የሚገኙ ሶስት የምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ክስ እንዲመሰረት ቦርዱ ለፌደራል ፖሊስ ጥያቄ ማቅረቡንም አስረድተዋል።
በተሁልደሬ 1 እና ተሁልደሬ 2 የምርጫ ክልሎች ላይ የተፈጠረውን ችግር ፖሊስ በምርመራ እንዲያጣራ ቦርዱ መጠየቁንም የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊዋ አክለዋል። በአማራ ክልል በመተማ የምርጫ ክልል እና በደቡብ ክልል ስቄ 1 እና ስቄ 2 የምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ የምርጫ ቁሳቁሶች እና ሰነድ ማሸጊያ የሆነው ሰማያዊ ሳጥን በምርጫ አስፈጻሚዎች ቢከፈትም፤ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ባለመነካካታቸው በእነዚህ ቦታዎች ምርጫው እንደሚካሄድ ሶልያና አብራርተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በሚገኘው ነገሌ የምርጫ ክልል፤ ነገ ድምጽ የማይሰጥበት ምክንያት በምርጫ ክልሉ ከተመዘገቡ አንድ የግል ዕጩ ጋር በተያያዘ እንደሆነ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል። የግል ዕጩው በምርጫ ክልሉ ለመወዳደር ከምርጫ ቦርድ የዕውቅና ሰርተፊኬት ቢሰጣቸውም “በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ አልተካተትኩም” ብለው ባቀረቡት አቤቱታ ምክንያት ቦርዱ ጉዳዩን ለማጣራት በሚል በቦታው ምርጫ እንዳይካሄድ መወሰኑን ሶልያና ተናግረዋል።
ቦርዱ ከዚህ በፊት በመራጮች ምዝገባ አለመከናወን፣ በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ላይ በተፈጠረ እክል እና ቦርዱ ከፓርቲዎች ጋር ባሉበት የፍርድ ቤት ሙግቶች ምክንያት በ64 የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ድምጽ እንደማይሰጥ አስታውቆ ነበር። ምርጫ ቦርድ ዛሬ በአምስት የምርጫ ክልሎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ፤ ሰኔ 14 ድምጽ የማይሰጥባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ቁጥርን ወደ 69 ከፍ አድርጎታል። በዚህም መሰረት ከሰዓታት በኋላ በሚጀመረው ስድስተኛው ሀገራዊ ለምርጫ ውድድር የሚቀርቡት የፓርላማ መቀመጫዎች ብዛት ወደ 440 ዝቅ ብሏል።

ምርጫው ወደማይካሄድባቸው አምስት የምርጫ ክልሎች የተጓጓዘው “የምስጢራዊው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?” ተብለው በጋዜጠኞች የተጠየቁት ሶልያና፤ “ወረቀቶቹ ወደ ማዕከል ይመለሱ ወይስ እዛው ይቆዩ የሚለውን እስካሁን አልወሰንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ማንኛውም [የመንግስት መዋቅር] በታችኛው እርከን ላይ ያለ ግለሰብ፤ ‘[ተወዳዳሪ] ዕጩው ማነው? ድምፅ መስጫ ወረቀቱ ምን አይነት ነው?’ ብሎ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ከፍቶ ማየት አይችልም” ሲሉ የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አስጠንቅቀዋል። “የድምጽ መስጫ ወረቀቶች የታሸጉባቸውን ሳጥኖች ማንቀሳቀስ እና መክፈት ወደ ድጋሚ ምርጫ ነው የሚመራን” ሲሉም ይህ አካሄድ የሚያስከትለውን ችግር በመጥቀስ የመንግስት ኃላፊዎችም ሆኑ ምርጫ አስፈጻሚዎች ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡ አሳስበዋል።
ምርጫ ቦርድ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ፤ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው አቤቱታዎች ናቸው። “ ‘ምርጫው አንድ ቀን ሲቀረው ዕጩ ቀይረን ነበር’ የሚሉ የፓርቲዎችን አቤቱታዎች ቦርዱ ሙሉ በሙሉ ቦርዱ አልተቀበለውም” ሲሉ ሶልያና ተናግረዋል።
ቦርዱ የፖርቲዎችን አቤቱታ ያልተቀበለው፤ በሶስት የተለያዩ ወቅቶች የዕጩዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጎ፣ ፓርቲዎችም ፈርመው በማጽደቃቸው መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊዋ አስረድተዋል። በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች አደራደር የሎተሪ ዕጣ ሲወጣ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበው ገንዘብ በተከፋፈለበት ወቅት እንዲሁም ከአንድ ሳምንት በፊት በነበረ ሌላ ሁነት የዕጩዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጎ እንደነበርም ዘርዝረዋል።
በምርጫው ዕለት ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎች የሚስተናገዱት በቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች እንደሆኑ የጠቆሙት ሶልያና፤ እነዚህን ኮሚቴዎች የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች በምርጫው ዕለት ማቋቋም እንዳለባቸው አብራርተዋል። የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው ሶስት አባላት የሚኖሩት ሲሆን የፖልቲካ ፓርቲዎች ቅሬታዎችን ተቀብሎ የማስተናድ ኃላፊነት ተጥሎበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)