በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ድምጽ ከማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች ዝርዝር ውስጥ አካትቶት በነበረው የነገሌ ምርጫ ክልል፤ በዕለቱ ምርጫ ሲካሄድ መዋሉን አስታወቀ። የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በሚገኘው የነገሌ ምርጫ ክልል ከ100 በላይ በሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች ሰኔ 14 ድምጽ ሲሰጥ ነበር።
የቦርዱ ሰብሳቢ ዛሬ ሐሙስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ምርጫው የተካሄደው የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ወይም የቦርዱ ሰራተኛ ምርጫ ይካሄዳል በማለቱ ነው ብለዋል። “ለፌደራል ፖሊስ አሳውቀን፤ ጥፋቱ የማን እንደሆነ እናጣራለን፤ በህግም እንጠይቃለን” ሲሉም ውሳኔውን የወሰነው ግለሰብ ተጠያቂ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ቦርዱ በምርጫው ዋዜማ እሁድ ሰኔ 13 በሰጠው መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የነገሌ ምርጫ ክልልን ጨምሮ በሌሎች አምስት የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጠት ሂደቱ ወደ ጷጉሜ 1 መዛወሩን አስታውቆ ነበር። የነገሌ ምርጫ ክልል ድምጽ አሰጣጥ የተራዘመበት ምክንያት፤ በምርጫ ክልሉ የሚወዳደሩ እና ከቦርዱ የምስክር ወረቀት ያገኙ የግል ዕጩ በተወዳዳሪዎች ዝርዝር ውስጥ አለመካተታቸው እንደሆነ የቦርዱ ሰብሳቢ በወቅቱ ገልጸው ነበር።
ሰብሳቢዋ በዛሬው መግለጫቸው፤ ሰኔ 14 በነገሌ የምርጫ ክልል የተካሄደውን ምርጫ “ህገ ወጥ” ሲሉ ጠርተውታል። ቦርዱ የምርጫውን ውጤትም እንደማይቀበለው ተናግረዋል።
ምርጫ ቦርድ በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ዛሬ በሰጠው መግለጫ አብዛኛውን ጊዜ ወስዶ የነበረው ጉዳይ፤ አጠቃላይ የምርጫውን ውጤት የማጠቃለል እና የማሳወቅ ሂደት ነው። የቦርዱ ሰብሳቢ “ብዙዎቹ ውጤቶች ከምርጫ ጣቢያ ወደ ምርጫ ክልሎች ተልከዋል” ሲሉ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ አመልክተዋል።
በአማራ፣ በሲዳማ እና አፋር ክልሎች ያሉ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች፤ የምርጫ ውጤት የያዙ ሰነዶችን ወደ ምርጫ ክልሎች አለመላካቸውን ጨምረው አስታውቀዋል። ለሰነዶቹ መጓጓዝ መዘግየት ዋና ምክንያቱ የምርጫ ጣቢያዎቹ ከምርጫ ክልሉ ማዕከል ያላቸው ረዥም ርቀት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል ያሉት ምርጫ ጣቢያዎች ያሉበት አካባቢ “ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ” ውጤቶች የተመዘገቡባቸውን ሰነዶች በማጓጓዝ ረገድ መዘግየት መታየቱን አክለዋል። በአዲስ አበባ ከተማ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች ካሉ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ውጤት አዳምረው የገለጹ መኖራቸውን ብርቱካን ጠቁመዋል። በምርጫ ክልሎቹ ይፋ የተደረገው ውጤት “ጊዜያዊ” መሆኑንም ከግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ከውጤት ማዳመር ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን መስተዋሉንም በዛሬው መግለጫቸው አንስተዋል። እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት፤ ወደ አጠቃላይ የውጤት ቋት ውስጥ የማይገቡ እና ኳራንታይን የተደረጉ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ መሆናቸውን ብርቱካን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ከእነዚህ ውጭ ባሉና እንከን በተፈጠረባቸው ሌሎች የምርጫ ጣቢያዎች፤ ያልታረቁ ቁጥሮችን እንደገና የመቁጠር እና ሰነድ ማመሳከር ስራ ይሰራልም ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)