የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ መቐለ የሚያደርገውን በረራ ላልተወሰነ ጊዜ አቋረጠ

በበእምነት ወንድወሰን  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትግራይ እንደገና ባገረሸው ውጊያ ምክንያት ወደ መቐለ የሚያደረገውን የመንገደኞች የበረራ አገልግሎት አቋረጠ። አየር መንገዱ በረራውን ያቋረጠው ከማክሰኞ ሰኔ 15 ጠዋት ጀምሮ እንደሆነ የድርጅቱ እና የጉዞ ወኪል  ሰራተኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በትላንትናው እና በዛሬው ዕለት ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ፤ ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ በረራ የነበራቸው መንገደኞች ከጉዟቸው መስተጓጎላቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከተጓዦቹ አረጋግጣለች። ለተጓዦቹ በረራ መሰረዙ የሚነገራቸው አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ እንደሆነ በመቐለ አየር ማረፊያ የሚሰሩ አንድ ባለሙያ ገልጸዋል። “ጉዳዩ የደህንነት ጉዳይ ስለሆነ ለሰራተኞችም የሚነገረው በድንገት ነው ሲሉ እኚሁ ባለሙያ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትግራይ ክልል ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ ለአንድ ወር ከግማሽ አቋርጦት የነበረውን በረራ የጀመረው በታህሳስ ወር አጋማሽ ነበር። አየር መነገዱ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ወደ መቐለ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ በቀን እስከ አምስት ጊዜ በረራዎችን ያደርጋል። አየር መንገዱ ለእነዚህ በረራዎቹ ከ80 እስከ 85 ሰዎችን የማጓጓዝ አቅም ያላቸው በመጠን አነስ የሚሉ አውሮፕላኖች እና እስከ 200 ያህል ሰዎችን የመጫን ያላቸውን በመጠን ተለቅ ያሉ አውሮፕላኖችን ይጠቀማል። 

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ የመጨረሻው በረራ የተደረገው 53 ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከመቐለ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ወደ አዲስ አበባ ማክሰኞ ከምሽቱ 12 ጉዞውን ባደረገው አውሮፕላን ነው። ከዚያ በኋላ የነበሩት በረራዎች የተቋረጡት፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ አንድ የጦር አውሮፕላን ግጀት በተባለ አካባቢ በአየር ላይ ተመትቷል መባሉን ተከትሎ መሆኑን እኚሁ የአየር መንገዱ ሰራተኛ ያብራራሉ። 

በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል በእሳት የተያያዘ አንድ አውሮፕላን ወደ መሬት ሲወርድ አሳይቷል። አውሮፕላኑ በትግራይ አማጽያን በአየር መቃወሚያ መመታቱ ቢገለጽም፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቃል አቃባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ይህንን አስተባብለዋል። “አውሮፕላኑ የወደቀው በቴክኒክ ችግር ነው። ብልሽት እንዳለው አሳይቶ ነው የወደቀው” ሲሉ ኮሎኔል ጌትነት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ከዚህ ቀደምም “አንቶኖቭ አውሮፕላን ሊያርፍ ሲል በቴክኒክ ችግር ምክንያት እንደዚህ ሆኖብን ያውቃል” የሚሉት ቃል አቃባዩ፤ እንዲህ አይነት ችግሮች በሌሎች ሀገራትም የሚከሰት መሆኑን ይገልጻሉ። “የተመረጡ፣ ለህዝብ ትርኢት ሊያሳዩ የወጡ አውሮፕላኖች ጭምር፤ ትርኢት እያሳዩ ይወድቃሉ” ሲሉም ገለጻቸውን በምሳሌ አስደግፈዋል። 

በጦር አውሮፕላኑ ላይ አደጋው ከደረሰ በኋላ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አውሮፕላኖች ወደ አካባቢው የሚያደርጉትን በረራ አቋርጠው እንደው የተጠየቁት ኮሎኔል ጌትነት፤ “የኢትዮጵያ አየር ኃይል የትኛውም ቦታ ሄዶ የመምታት አቅም አለው። ምንም ጥያቄ በሌለው በየትኛውም ቦታ ላይ ይበራል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የመንገደኞች በራርን መቋረጥን አስመልክቶ ማብራሪያ ለማግኘት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን አላገኘም። የክፍሉ ኃላፊም ጥያቄውን ለበላይ አካላት እንዳስተላለፉ ነገር ግን እስካሁን ከበላይ ያገኙት የተሰጣቸው ምላሽ እንደሌለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳደር” ተናግረዋል። የአየር መንገዱ ሰራተኞች ግን “በረራዎች መቼ እንደሚጀመሩ እስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም” ብለዋል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ተስፋለም ወልደየስ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]