በሃሚድ አወል
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በፈታኝ እና ችግር ባለበት ሁኔታ እንዲሁም በተገደበ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ መካሄዱን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ እና 13 ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ። ምርጫው የተካሄደው፤ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እስር፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መዋከብ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት ቅስቀሳ ለማድረግ አለመቻልን ጨምሮ ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉበት ነው ብለዋል ሀገራቱ።
በአዲስ አበባ የሚገኙ የጀርመን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ ኤምባሲዎችን ጭምር ያካተተው መግለጫው፤ በምርጫው ሂደት ላይ የተስተዋሉ ስኬቶችን፣ ተግዳሮት እና ጉድለቶችን በግልጽ ማሳወቅ ወደ ፊት ለሚደረጉ ምርጫዎች መሻሻል እንደሚረዳ ጠቅሷል። በምርጫ ህጉ ላይ አስፈላጊ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን እና በምርጫ ሂደቱ ውስጥ ታማኝነትን ለማዳበር ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራት እና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ለመወያየት በምርጫ ቦርድ የተወሰዱ አዎንታዊ እርምጃዎች እንደነበሩ እውቅና ሰጥቷል።
![](https://ethiopiainsider.com/wp-content/uploads/2021/06/Polling-day-at-Kazanchis-Addis-Ababa.jpg)
በምርጫው ዕለት በርካታ ሰዎች ምሽቱንም ጭምር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በመቆየት የድምጽ መስጠት ሂደቱ እንዲከናወን ማድረጋቸውን መግለጫው አንስቷል። የምርጫ ውጤት የማሳወቅ ሂደቱ እና ስራው አሁንም እንደቀጠለ ያመለከተው መግለጫው፤ እንዲያም ቢሆን በምርጫ ሂደቱ ውስጥ የተስተዋሉ በርካታ የአሰራር ችግሮች አሉ ብሏል መግለጫው።
ምርጫው በፈታኝ እና ችግር ባለበት ሁኔታ መካሄዱን የጠቆመው መግለጫው፤ በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች አሳሳቢ የጸጥታ ሁኔታዎች እንዳሉ አመልክቷል። ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ለመምረጥ አለመመዝገባቸው እና በምርጫው በሚገባ አለመካተታቸው መግለጫው በትኩረት ካነሳቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። በምርጫው የተወዳደሩ ሴቶች ቁጥር ካለፈው አጠቃላይ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሶስተኛ መቀነሱንም መግለጫው አጽንኦት ሰጥቶታል።
![](https://ethiopiainsider.com/wp-content/uploads/2021/06/Polling-Day-June-21-2021.jpg)
“ምርጫ ብቻውን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ አያመጣም። እያጋጠሙ ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮችንም አይፈታም” ያለው የሀገራቱ መግለጫ፤ መንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትርጉም ያለው መጠነ ሰፊ የብሔራዊ ውይይት ሂደት መካሔዱን እንዲያረጋግጡ እና ለሰላማዊ መፍትሄ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጠይቋል።
ውይይቱ በመላ ሀገሪቱ ግጭትን ለመቀነስ እና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ እድገትን ለማስቻል አስፈላጊ መሆኑን የጋራ መግለጫው አስታውቋል። በትግራይ ላለው ሁኔታም ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚበጅም አስገንዝቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)