እስካሁን የምርጫ ውጤት ያሳወቁ የምርጫ ክልሎች ግማሽ ያህሉ መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ከተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች እስካሁን ውጤት ያሳወቁት ግማሽ ያህሉ መሆናቸውን ገለጸ። ውጤት ካሳወቁ የምርጫ ክልሎች ውስጥ አብዛኞቹ የሚገኙት በኦሮሚያ ክልል መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 19 ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ባለፈው ሰኞ ምርጫ ከተካሄደባቸው 440 የምርጫ ክልሎች ውስጥ እስካሁን ውጤት ያሳወቁት 221 የምርጫ ክልሎች ናቸው። ውጤት ካሳወቁ የምርጫ ክልሎች ውስጥ 125ቱ የሚገኙት በኦሮሚያ ክልል መሆኑንም ኃላፊዋ ገልጸዋል። 

በአማራ ክልል ምርጫ ከተካሄደባቸው 125 ምርጫ ክልሎች እስካሁን ውጤት ያሳወቁት 40 ገደማ ብቻ መሆናቸውን ያስረዱት ሶልያና፤  በአዲስ አበባ ካሉት 23 የምርጫ ክልሎች ደግሞ እስካሁን ውጤት ያሳወቁት 10 ብቻ ናቸው ብለዋል። ቦርዱ በማዕከል ደረጃ እስካሁን አረጋግጦ ሰርተፍኬት የሰጠው ለሰባት ወይም ለስምንት ምርጫ ክልሎች ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በምርጫ ክልል ደረጃ ይፋ የሚደረገው ውጤት እንዲዘገይ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ከምርጫ ጣቢያ ወደ ምርጫ ክልል ውጤት ለማድረስ የሚያጋጥሟቸው ችግር አንዱ መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ተናግረዋል። የድምጽ ቆጠራው በአንድ ቀን ያላለቀላቸው ምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው እንዲሁም ወደ ምርጫ ክልል ተሞልተው መምጣት ያለባቸው ፎርሞች በትክክል ተሞልተው አለመምጣታቸው፤ ውጤቱ በምርጫ ክልል ደረጃ ለማሳወቅ መዘግየት መፍጠሩን አብራርተዋል። 

በምርጫ ክልል ደረጃ ድምጾች እንደገና እየተቆጠሩ መሆኑንም ኃላፊዋ በዛሬው መግለጫቸው አንስተዋል። “በምርጫ ክልል ደረጃ ያለ ትክከለኛነት በጣም አስፈላጊ ነው” ያሉት ሶልያና፤ ምርጫ ክልሎች እንከኖችን ሲያገኙ የውጤቱን ትክከለኛነት ለማረጋገጥ ሲባል ውጤቶችን እንደገና ይቆጥራሉ ብለዋል። 

“ምርጫ ክልሎች፤ ዛሬ ማምሻውን በጣም ገፋ ከተባለ ግን ነገ [ውጤት] አሳውቀው መጨረስ አለባቸው” ሲሉም አክለዋል። ጋምቤላ እና ሲዳማ ክልሎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን አንድ ቀን ዘግይተው ስለጨረሱ፤ ውጤት ማሳወቂያ አንድ ተጨማሪ ቀን እንደሚኖራቸውም ጨምረው ገልጸዋል። 

የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ በዛሬው መግለጫው ያነሱት ሌላው አበይት ጉዳይ፤ በድሬዳዋ ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች የተመለከተ አዲስ መረጃን ነው። ኃላፊዋ በድሬዳዋ ስድስት ምርጫ ጣቢያዎች ሰኔ 14 የክልል ምክር ቤት ምርጫ አለመካሄዱን ተናግረዋል። የከተማይቱ የምርጫ ክልል ኃላፊ በዕለቱ ለክልል ምክር ቤት ድምጽ ያልተሰጠው፤ “የክልል ምክር ቤት ድምጽ መስጫ ወረቀት ባለመድረሱ ነው” ማለታቸውን ሶልያና አስረድተዋል።  

ስድስቱ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በትክክለኛው መንገድ ያልተከናወነባቸው ተብለው ከዚህ ቀደም በቦርዱ የተለዩ ነበሩ። በምርጫ ጣቢያዎቹ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳዳረው አንድ ፓርቲ መሆኑን የተናገሩት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊዋ፤ “በክልል ምክር ቤት የሚኖረውን ውጤት አይቀይረውም። ስለዚህ [በምርጫ ጣቢያዎቹ] ምንም አይነት ተጨማሪ ምርጫ ማካሄድ አያስፈልግም ብሎ ቦርዱ ወስኗል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  

በድሬዳዋ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ፤ በልዩ ሁኔታ የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ አለመካሄዱን ሶልያና ገልጸዋል። የዚህን ምርጫ ጣቢያ ጉዳይ በተመለከተ “በአጠቃላይ የተወካዮች ምክር ቤት ውጤት ታይቶ ውጤቱን የሚቀይር ከሆነ፤ ተጨማሪ ውሳኔ ቦርዱ የሚወስን ይሆናል” ብለዋል። ለተፈጠረው የምርጫ መስተጓጉል “ኃላፊነት የሚወስደው ማነው?” የሚለውን በተመለከተ፤ የምርጫ ክልሉ እና የቦርዱ ድሬዳዋ ጽህፈት ቤት ማጣራት እያደረገ መሆኑን ኃላፊዋ አመልክተዋል። 

ከድምጽ ቆጠራ ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልል ቁጫ ምርጫ ክልል የሚካሔደው ቆጠራ እንዲቋረጥ መደረጉንም ሶልያና በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል። “በምርጫ ክልሉ የሚከናወነው ቆጠራና ውጤት ማዳመር የፓርቲ ወኪሎች እና የቦርዱ ምርጫ አስፈጻሚዎች በሌሉበት ነው እየተከናወነ ያለው” የሚሉ አቤቱታዎች መቅረባቸውን የተናገሩት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዋ፤ “በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ በሂደቱ ላይ ጥላ ሚያጠላ በመሆኑ የውጤት ቆጠራ እና ማደመር እንዲቋረጥ ተደርጓል” ብለዋል። ቦርዱ የምርጫ ቁሳቁሶች ታሽገው እንዲጠበቁ ማድረጉንም አስረድተዋል።  

ምርጫ ቦርድ በድምጽ መስጫው ዕለት የተፈጠሩ ችግሮችን በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ከስር ከስር እያየ ለመፍታት መሞከሩን ሶልያና በዛሬው መግለጫቸው ጠቅሰዋል። ቦርዱ ከምርጫው ቀን በኋላ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚቀርቡለት አቤቱታዎች ውሳኔ የሚሰጠው፤ አቤቱታዎቹ የቀረቡባቸው ምርጫ ክልሎች፣ በምርጫ ክልሎቹ የተፈጠሩት የአሰራር ግድፈቶች እና እነዚህ የአሰራር ግድፈቶች በውጤቱ ላይ የሚያመጡትን ለውጥ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነው ሲሉ አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)