የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች መቐለ ከተማን ለቅቀው መውጣታቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ተናገሩ

በተስፋለም ወልደየስ

በመቐለ ከተማ የሚገኙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እና የፌደራል ፖሊሶች ዛሬ ሰኞ ከሰዓት ከተማይቱን ሙሉ ለሙሉ ለቅቀው መውጣታቸውን ስድስት የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የጸጥታ አስከባሪ አካላቱ መቐለን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የትግራይ አማጽያን ወደ ከተማይቱ መግባት መጀመራቸውን እንደሰሙ የዓይን እማኞቹ ገልጸዋል።    

የፌደራል መንግስት የጸጥታ ሃይሎች፤ በወታደራዊ እና በሲቪል ተሽከርካሪዎች በመሆን በኩዊሃ አቅጣጫ መቐለን ለቅቀው መውጣት የጀመሩት ዛሬ ከእኩለ ቀን በኋላ መሆኑን የዓይን እማኞቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ተሽከርካሪዎቹ ከከተማይቱ ሲወጡ በመስመር ተከታትለው እንደነበር የተናገሩት የአይን እማኞች በላይቸው ላይም መትረየስን ጨምሮ ሌሎችም ከባድ መሳሪያዎችን በተጠንቀቅ የደቀኑ ወታደሮች ተጭነው ነበር ብለዋል።  

የአፋር ክልልን ከትግራይ ጋር በምታዋስነው አብ አላ ከተማ የሚገኙ አንድ ነዋሪ፤ ብዙ ወታደሮችን የጫኑ እና በሸራ የተከለሉ ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ መመልከታቸውን ተናግረዋል። አንድ የሰመራ ነዋሪም በተመሳሳይ መልኩ በርከት ያሉ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አመሻሹን ወደ አፋር ክልል ዋና ከተማ ሲገቡ አይቼያለሁ ብለዋል። 

በመቐለ ሆቴሎችን፣ ባንኮችን እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ሲጠብቁ የነበሩ የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ምድብ ቦታቸው ለቅቀው መሄዳቸው የአይን እማኞች ጠቁመዋል። በመቐለ የሚገኝ እና የመንግስት ባለስልጣናት በሚያዘወትሩት ሆቴል የሚሰራ አንድ ግለሰብ፤ ለሆቴሉ ጥበቃ የሚያደርጉ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከዛሬ ረፋድ አራት ሰዓት ገደማ ጀምሮ ወደ ከተማ ከሄዱ በኋላ አለመመለሳቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። “ሆቴሉን እኛው ራሳችን እየጠበቅን ነው ያለነው” ሲል ይሄው የሆቴሉ ሰራተኛ አክሏል።   

በመቐለ ዛሬ ከሰዓት የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር የተናገሩት የዓይን እማኞች፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይም የዘረፋ ሙከራዎች ነበሩ ብለዋል። “የትግራይ ተዋጊዎች ወደ ከተማው እየገቡ ነው” መባሉን ተከትሎ አመሻሽ ላይ በርካቶች የትግራይ እና የህወሓት ባንዲራን በመያዝ ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር ተብሏል።

በአይደር ሆስፒታል አካባቢ የሚገኙ አንድ የዓይን እማኝ፤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የአካባቢው ነዋሪዎች ደስታቸውን በጩኸት፣ በዘፈን እና በርችት በማጀብ እየገለጹ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “ሰማይ ላይ ርችት ይታያል። በመኪናም፣ ዘፈን ከፍተው፣ ክላክስ [የመኪና ጡሩምባ] እያሰሙ እየሄዱ ነው” ሲሉ በአካባቢያቸው ያለውን ድባብ ገልጸዋል።     

ብዙዎች የከተማይቱ ነዋሪዎች በጸጥታ ስጋት ምክንያት በሰፈራቸው ተሰብስበው የሚሆነውን በቅርበት በመከታተል ላይ እንዳሉም አመልክተዋል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ይጠቀምበት የነበረው የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ስርጭቱን ማቋረጡንም የዓይን እማኞቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች መቐለ ከተማን ለቅቀው ወጥተዋል ስለመባሉ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቃል አቃባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነን ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም ሳይሳካልን ቀርቷል። ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ተመሳሳይ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ለዚህ ዘገባ በእምነት ወንድወሰን አስተዋጽኦ አድርጋለች። በዚህ ዘገባ ላይ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል።]