የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላለፈ

በተስፋለም ወልደየስ   

የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉም የፌዴራል እና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ ማዘዙን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ምሽቱን ባወጣው መግለጫ “ይሄን መልካም ዕድል ለክፉ የሚጠቀሙ ወገኖች ካጋጠሙ ግን አስፈላጊው ሕግን የማስከበር ተግባር እንደ አግባቡ የሚከናወን ይሆናል”  ሲል አስጠንቅቋል።

የተኩስ አቁሙ “በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ” እንደሆነ የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት፤ ተፈጻሚነቱም “ያለ ቅድመ ሁኔታ” የሚከናወን መሆኑን ይፋ አድርጓል። ከዛሬ ሰኞ ሰኔ 21፤ 2013 ጀምሮ እስከ እርሻ ወቅት ማጠናቀቂያ ድረስ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የተኩስ አቁሙ፤ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል “በተናጠል” የሚፈጸም እንደሆነም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔውን ለማስተላለፍ መነሻ ምክንያት ከሆኑት መካከል በትግራይ ያለው አርሶ አደር “ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዲከውን” እንዲሁም “የእርዳታ ስራው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሰራጭ” በማሰብ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ አመልክቷል። ጽህፈት ቤቱ “ሰላምን የሚመርጡ የሕወሓት ርዝራዥ” ሲል የጠራችው አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ የተኩስ አቁሙ እንደሚያስችላቸው ጠቁሞ፤ እነዚህን ኃይሎች “ባለማወቅ” ተከተሉ ያላቸው ግለሰቦችም “እንደገና ለማሰብና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ዕድል እንዲያገኙ” ያስችላል ብሏል። 

የፌደራል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁሙን ያወጀው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ በመቀበል እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ ጠቁሟል። “በትግራይ ክልል ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ወዳጆች ሲቀርቡ የነበሩ የመፍትሔ ሃሳቦችን የፌደራል መንግስት ሲያጤናቸው ቆይቷል” ብሏል መግለጫው። ከዚህ ባሻገርም “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተከታታይ ያቀረበውን ጥያቄ መንግስት ከተለያየ አቅጣጫ ተመልክቶታል” ሲልም መግለጫው ያትታል። 

ከዚህ መግለጫ ደቂቃዎች ቀደም ብሎ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረቡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ፤ የፌደራል መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ መጠየቃቸውን አስታውቀው ነበር። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥያቄውን በይፋ ያቀረበው ባለፈው ሳምንት መሆኑን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ “መንግስት ሆደ ሰፊ ሆኖ ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን መስጠት ይጠበቅበታል” ማለቱም ተዘግቧል። 

በትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ ወደሚፈለገው ቦታ እንዲደርስ፣ አርሶ አደሩ በክረምቱ ወራት ወደ እርሻው እንዲገባ እና ከቀያቸው የተፈናቀሉት ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ “ተጨማሪ ፖለቲካዊ አማራጭ” ማስፈለጉን ዶ/ር አብርሃም ተናግረዋል ተብሏል። በእነዚህ ምክንያቶችም ጊዜያዊ አስተዳደሩ “በተደጋጋሚ ከመንግስት ጋር ንግግር ማድረጉን” ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል። “በአሁኑ ወቅት ከህወሓት ሃይሎች መካከል የሰላም መንገድ የሚፈልጉ አሉ” ያሉት ዶ/ር አብርሃም፤ ለእነዚህ ሃይሎች እድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸው በዘገባው ተካትቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ምሽቱን ባወጣው መግለጫም የዋና ስራ አስፈጻሚውን ገለጻ አስተጋብቷል። “የሕወሓት የጥፋት ኃይል በሚነዛው ሽብር የተነሳ ሕዝቡ የጦርነት ጋሻ ሆኖ እየተማገደ ይገኛል። ሲዋጋ ሚሊሺያ፤ ሲጠቃ ሲቪል የሚሆን ኃይል እየተፈጠረ ነው። በዚህ የተነሣ ሕወሓት በፈጠረው ቀውስ ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ እርሻቸው የተስተጓጎለባቸው፣ አካባቢያቸውን ለቅቀው የተፈናቀሉ ሁሉ የተረጋጋ ኑሮ ለመኖር አልቻሉም” ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ ከስሷል። 

“በአንድ በኩል እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በረሃ ከተበተነው ኃይል ውስጥ ሁኔታዎች ቢመቻቹለት ወደ ሰላም ሊመጣ የሚችል ኃይል ይኖራል ተብሎ ስለታመነ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጥያቄ መንግስት በአዎንታዊነት ተቀብሎታል” ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[ለዚህ ዘገባ ሃሚድ አወል አስተዋጽኦ አድርጓል]