በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የተቆጠሩ ምስክሮች በክፍት ችሎት እንዲሰሙ ተወሰነ

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ህግ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የቆጠራቸው 16 ምስክሮች በክፍት ችሎት እንዲሰሙ ወሰነ። የከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 22፤ 2013 ውሳኔውን ያሳለፈው፤ ምስክሮች “ለደህንነታቸው” ሲባል በዝግ ችሎት ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙ በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ነው።

ፍርድ ቤቱ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የተቆጠሩትን 16 ምስክሮች በአምስት ቀናት ውስጥ እንደሚሰማ አስታውቋል። ምስክሮችን ለመስማትም ለሐምሌ 8፣ 9፣ 14፣ 15 እና 16 ቀጠሮ ሰጥቷል። ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡት አራት ተከሳሾች ውስጥ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል እና አስቴር ስዩም ከፍርድ መጓተት እና ከማረሚያ ቤት ጋር የተያያዙ አቤቱታዎችን አቅርበዋል።

በዛሬው የችሎት ውሎ በርከት ያሉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ደጋፊዎች ለተከሳሾች ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በችሎቱ ተገኝተዋል። ከችሎቱ ማብቃት በኋላም ተከሳሾቹ እና ደጋፊዎቻቸው መጠነኛ መፈክር አሰምተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)