በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሶስት የተወካዮች ምክር ቤት እና 29 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ውጤት ዛሬ ይፋ አደረገ። ቦርዱ አረጋግጦ ይፋ ያደረጋቸው፤ ሰኔ 14 በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በሚገኙ አስር የምርጫ ክልሎች የተካሄዱ ድምር የምርጫ ውጤቶችን ነው።
በዛሬው የምርጫ ቦርድ ውጤት መሰረት ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ፤ በአማራ ክልል በሚገኘው የጢስ አባይ ምርጫ ክልል የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፏል። የጢስ አባይ ምርጫ ክልል፤ አንድ የተወካዮች ምክር ቤት እና ሁለት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን በስሩ 74 የምርጫ ጣቢያዎችን ይዟል።
በዚህ የምርጫ ክልል ለመምረጥ ከተመዘገቡት መራጮች ውስጥ፤ ሰኔ 14 በመራጮች መዝገብ ላይ ፊርማቸውን አስፍረው ድምጽ የሰጡት ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን በቦርዱ ድምር ውጤት ላይ ተመላክቷል። በጢስ አባይ ምርጫ ክልል የመኢአድ፣ እናት፣ ኢዜማ፣ አብን፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ እና ብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች ተፎካክረዋል።
ዛሬ ይፋ በተደረጉት የኦሮሚያ ክልል ዘጠኝ የምርጫ ክልሎች ውጤት ገዢው የብልጽግና ፓርቲ በለስ ቀንቶታል። ከዘጠኙ የምርጫ ክልሎች ውስጥ በስምንቱ ገዢው ፓርቲ ብቻውን ነው የተወዳደረው። ሶስት የክልል ምክር ቤት መቀመጫ ባለው ጮራ በተባለው የምርጫ ክልል፤ ኢዜማ ዕጩውን ቢያቀርብም ገዢውን ፓርቲ መገዳደር ሳይችል ቀርቷል።
ከዘጠኙ የምርጫ ክልሎች አንዱ የሆነው “ጭሮ ሶስት”፤ ከክልል ምክር ቤት ውጤት በተጨማሪ በምርጫ ክልሉ የፓርላማ መቀመጫውን ያሸነፈው ፓርቲም ታውቋል። በሌሎቹ የምርጫ ክልሎች እንደታየው ሁሉ በብቸኝነት የቀረበው ብልጽግና ፓርቲ፤ የምርጫ ክልሉን አንድ የፓርላማ እና ሶስት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ያለተቀናቃኝ አሸንፏል። በተመሳሳይም ዛሬ ውጤቱ በተነገረው የበደሌ የምርጫ ክልልም፤ የፓርላማ መቀመጫ አሸናፊው ገዢው ፓርቲ ሆኗል።
የመጀመሪያው የምርጫ ውጤት ይፋ በተደረገበት በዛሬው የምርጫ ቦርድ መግለጫ ላይ፤ እስካሁን ወደ ማዕከል የተላኩ የምርጫ ውጤቶች ብዛትም በቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አማካኝነት ተገልጿል። የቦርዱ ሰብሳቢ በዛሬው መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ ሰኔ 14 ድምጽ ከተሰጠባቸው 942 የተወካዮች እና ክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ውስጥ፤ እስካሁን ወደ ማዕከል የገባው የ618 መቀመጫዎች ውጤት ነው።
የውጤት አገላለጽን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ ሁለት መንገዶችን እንደሚከተል የቦርድ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል። የመጀመሪያው የተረጋገጡ የምርጫ ክልል ውጤቶች ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አብይ የሆነ አቤቱታ ያልቀረበባቸውን የምርጫ ክልሎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ማሳወቅ ነው። የምርጫ ውጤቶች ማዳመርን በተመለከተም፤ መረጃዎች በስነ ስርዓት መሟላታቸውን እና ቁጥሮች እርስ በእርስ እንደማይጣረሱ የምናረጋግጥበት የህግ ስነ ስርዓት አለ ሲሉም በዛሬ መግለጫቸው ማስተማመኛ ሰጥተዋል።
ምርጫ ቦርድ የመጨረሻውን ውጤት ለህዝብ ይፋ ከማድረግ ሊያግደው የሚችለው ነገር የፓርቲዎች አቤቱታ መሆኑን ብርቱካን በዛሬው መግለጫቸው አንስተዋል። እስካሁን ድረስ በ160 የምርጫ ክልሎች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታዎችን ማቅረባቸውንም አስረድተዋል።
“160 [የምርጫ] ክልሎችን በሚመለከት ፓርቲዎች አቤቱታ አቅርበዋል ስንል፤ በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች ብዙ ፓርቲዎችም ያቀረቡባቸው አሉ። እነዚህን የፓርቲ አቤቱታዎች ቦርዱ በጣም በተፋጠነ ሁኔታ መፍታት እና ምላሽ መስጠት አለበት” ብለዋል የቦርድ ሰብሳቢዋ። ምርጫ ቦርድ ‘ተቀባይነት አላቸው’ ከሚላቸው አቤቱታዎች ውስጥ፤ “የምርጫውን ሂደት እና ውጤት በብዙ የማይነካ ከሆነ” እርሱን አረጋግጦ ለወደፊት ትምህርት የሚወስደው እንደሆነም አብራርተዋል።
“በትልቅ ደረጃ ውጤቱን ሊለውጥ ይችላል የሚባል ነገር በማጣራት ሂደታችን ካገኘን [ግን] ድጋሚ ምርጫ የምናደርግባቸው የምርጫ ክልሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በህጉ መሰረት እናውቃለን” ሲሉ እንደገና ምርጫ የሚደረግባቸው ቦታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥቆማ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በምርጫ ቦርድ ይፋ የተደረጉ የተወካዮች እና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ቁጥር ላይ ዘግየት ብሎ ማስተካከያ ተደርጓል]