የትግራይ አማጽያን የተኩስ አቁሙን እንዲቀበሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም “የትግራይ መከላከያ ኃይል” እየተባሉ የሚጠሩት አማጽያን “በፍጥነት እና ሙሉ በሙሉ” እንዲቀበሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠየቀ። የድርጅቱ የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በተናጠል ከሰኞ ሰኔ 21፤ 2013 ጀምሮ ያወጀውን የተኩስ አቁም “የትግራይ መከላከያ ኃይል በአፋጣኝ እና ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ እንዲያጸድቀው እንጠይቃለን” ብለዋል።

ሮዝሜሪ ይህን ያሉት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ትላንት አርብ ምሽት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረገው ግልጽ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። “የትግራይ መከላከያ ኃይል” እስካሁንም በተኩስ አቁሙ ላይ ስምምነቱን አለመግለጹን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ “የተኩስ አቁሙ ህወሓትን ጨምሮ በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች፤ ተቀብለው የሚቀጥሉበት ዕድል ሰጥቷል” ብለዋል። 

በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በበኩላቸው “ትርጉም ያለው የተኩስ አቁም፤ የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ክልል ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ለቅቀው መውጣታቸውን ያረጋግጣል“ ሲሉ ተደምጠዋል። ይኸው የተኩስ አቁም ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትን እንደሚያመቻች የተናገሩት አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ፤ “የኢትዮጵያ የውስጥም ሆነ የውጪ ድንበር በኃይል እና ሕገ-መንግስቱን በመጣስ እንደማይለወጡ ያረጋግጣል” በማለት ፋይዳውን አስረድተዋል። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ በግልጽ ሲወያይ የመጀመሪያው ነው። ከዚህ ቀደም ምክር ቤቱ ስድስት ጊዜ የተወያየ ቢሆንም ሁሉም በዝግ የተካሔዱ ነበሩ። በትላንቱ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ፤ የጸጥታው ምክር ቤት የፕሬዝዳንትነት ተራውን በተረከበችው ፈረንሳይ ተጋብዛ ተካፍላለች። 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ ታዬ አጽቀስላሴ በውይይቱ መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያን አቋም ለምክር ቤቱ አባላት አስደምጠዋል። አምባሳደር ታዬ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የውስጥ ጉዳያችን በመሆኑ ግልጽ ውይይት እንዲደረግበት ፍላጎታችን አልነበረም” ሲሉ ተናግረዋል።

የትላንት ምሽቱ የጸጥታው ምክር ቤት ውይይት ሲጀመር ማብራሪያ በመስጠት ቀዳሚ የሆኑት ሮዝሜሪ ዲካርሎ በአማራ ክልል ቁጥጥር ስር በሚገኘው ምዕራባዊ ትግራይ ምክንያት “ተጨማሪ ግጭት ሊቀሰቀስ እና የጸጥታ ሁኔታው በፍጥነት ሊያሽቆለቁል” እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። የኤርትራ ወታደሮች ወደ ድንበር አቅራቢያ መውጣታቸውን የገለጹት ኃላፊዋ “የትግራይ መከላከያ ኃይል” እየተባለ የሚጠራው አማጺ ቢገሰግስም የአማራ ክልል ኃይሎች አሁንም በምዕራባዊ ትግራይ እንደሚገኙ ገልጸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በትግራይ ከ400,000 ሺሕ በላይ ሰዎች ጠኔ ተብሎ ወደሚደበው የከፋ ረሐብ መሻገራቸውን፣ ሌሎች 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ከጠኔ አፋፍ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እና አስቸኳይ እርዳታ ጊዜያዊ አስተባባሪ ራሜሽ ራንጃሲንገም በንባብ ባሰሙት ንግግር ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

“ሰላሳ ሶስት ሺሕ ሕፃናት የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለባቸው። በመጪው ዝናባማ ወቅት የምግብ አቅርቦት ሲዳከም፣ የጎርፍ እና ኮሌራን ጨምሮ ውሃ ወለድ በሽታዎች ስጋቶች ሲጨምር ከዚህ የባሰ የምግብ ዋስትና ጉድለት ቀውሱ ይባባሳል” ያሉት ራሜሽ ራንጃሲንገም “በሰብዓዊ ዕርዳታ ካልደረስንላቸው በርካታ ሰዎች ይሞታሉ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

የእርዳታ አስተባባሪው የሁኔታውን ክብደት ለማስረዳት፤ ከ1,200 በላይ ወሲባዊ እና ፆታዊ ጥቃቶች ሪፖርት መደረጋቸውን፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ 12 የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሰራተኞች መገደላቸውን ጠቅሰዋል። በራሜሽ ራንጃሲንገም ማብራሪያ መሰረት ባለፉት ሁለት ወራት 3.7 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ ዕርዳታ ተቀብለዋል፣ 167,000 ተፈናቃዮች ምግብ ነክ ያልሆነ ዕገዛ ደርሷቸዋል። ለ630,000 ሰዎች ውሃ በመኪና ታድሏል። 

“ይሁንና በገጠራማው ትግራይ ባለፉት ስድስት ወራት 2.5 ሚሊዮን ሰዎች መሠረታዊ አገልግሎት አላገኙም። ይኸ ጠኔ የተጋረጠባቸውን በርካታ ሰዎች ይጨምራል። በአንድ በኩል ለጠኔ የተጋለጡትም በዚሁ ምክንያት ነው” ሲሉ የእርዳታ አስተባባሪው በክልሉ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ አብራርተዋል።

የምግብ እርዳታ ለፈላጊዎች ለማድረስ “ፈጣን እና ውጤታማ የጉዞ መስመር ሊፈቀድልን ይገባል” ያሉት የተመድ የእርዳታ አስተባባሪ፤ ከኮምቦልቻ እና ከሰመራ ወደ መቀሌ እንዲሁም ከጎንደር ወደ ሽሬ የሚወስዱ መንገዶች እንዲፈቀዱ ጠይቀዋል 

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለአንድ ሚሊዮን ሰዎች ለሚቀጥለው አንድ ወር የሚበቃ ምግብ በመቀሌ እንዳለው የገለጹት ራንጃሲንገም የምግብ እርዳታ ፈላጊው ቁጥር 5.2 ሚሊዮን በመሆኑ እንደማይበቃ ተናግረዋል። የምግብ እርዳታ ለፈላጊዎች ለማድረስ “ፈጣን እና ውጤታማ የጉዞ መስመር ሊፈቀድልን ይገባል” ያሉት የተመድ የእርዳታ አስተባባሪ፤ ከኮምቦልቻ እና ከሰመራ ወደ መቀሌ እንዲሁም ከጎንደር ወደ ሽሬ የሚወስዱ መንገዶች እንዲፈቀዱ ጠይቀዋል። 

የድርጅቱ የእርዳታ ማመላለሻ አውሮፕላን ዛሬ ቅዳሜ ወደ መቀሌ እንዲበር ከኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ ማግኘቱን የተናገሩት ራንጃሲንገም፤ እንዲህ አይነቱ በረራ በአንድ ብቻ እንዳይወሰን እና በትግራይ ወደሚገኙ ሁሉም  አየር ማረፊያዎች መብረር እንዲቻል ሊፈቀድ እንደሚገባም አሳስበዋል። የተለያዩ የሳተላይት መገናኛዎች ለግብረ ሰናይ አገልግሎት ማስገባት እንዲፈቀድም የተመድ የእርዳታ አስተባባሪ ጥያቄ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)