– ብልጽግና 8 ተጨማሪ የፓርላማ መቀመጫዎች ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ አግኝቷል
በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘጠኝ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ውጤቶችን አረጋግጦ ይፋ አደረገ፡፡ ቦርዱ ዛሬ ሰኔ 24፤ 2013 ይፋ ያደረገው በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ስምንት እና በአማራ ክልል የሚገኝ አንድ የፓርላማ መቀመጫ ውጤቶችን ነው፡፡
ስምንቱን የኦሮሚያ ክልል የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ብቻውን የተወዳደረው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል፡፡ በአማራ ክልል በእጅ ውሃ ምርጫ ክልል የፓርላማ ምርጫ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) እና ገዢው ብልጽግና ፓርቲ እጩዎቻቸውን አቅርበው ለፓርላማ ወንበር ተወዳድረዋል፡፡ ተቃዋሚው አብን የምርጫ ፉክክሩን አሸንፎ የተወካዮች ምክር ቤት ወንበሩን አግኝቷል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፤ በሰኔ 14 ለምርጫ የቀረቡት 440 ያህሉ ናቸው። በዕለቱ ምርጫ ከተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ እስካሁን ውጤታቸው የተገለጸው የ19ቱ ብቻ ነው።
ከእነዚህ የምርጫ ክልሎች ውስጥ፤ የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ውጤታቸው ይፋ የተደረገው የአስራ ሁለቱ ነው። እስካሁን ባለው የፓርላማ መቀመጫ ውጤት መሰረት፤ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን 10 መቀመጫዎች ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፤ በአማራ ክልል የሚገኙትን ሁለት መቀመጫዎች ደግሞ ተቃዋሚው አብን አብላጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፉን አረጋግጧል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)