በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ልጆች ያሏቸው ወላጆች አቤቱታቸውን አሰሙ

በሃሚድ አወል

በትግራይ ክልል የሚማሩ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ዛሬ ሐሙስ፤ ሰኔ 24 በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት እና በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ቢሮ በመገኘት አቤቱታቸውን አሰሙ። ወላጆቹ የመከላከያ ሰራዊት መቐለን ለቆ ከዋጣ በኋላ የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ የልጆቻቸውን ደህንነት ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችን በተመለከተ መንግስት መፍትሔ እንዲሰጣቸው የጠየቁት ወላጆቹ “ሰሚ ልናገኝ አልቻልንም፤ ልጆቻችንን የምናገኝበት መንገድ ይመቻችልን” ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። የፌደራል መንግስት ወታደሮችን ሲያስወጣ ተማሪዎቹን ችላ ብሏል በማለትም መንግስትን ወቅሰዋል።

ወላጆቹ ጉዳዩ ይመለከታዋል ካሉት የመንግስት መስሪያ ቤት በተጨማሪ፤ የተራድዖ ድርጅቶች በዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተማሪዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለሱ ስራ ላይ እንዲሳተፉ ለመማጸን ወደ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ቢሮ ደጃፍ ላይ በመገኘት ተማጽኗቸውን አቅርበዋል።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ ማምሻውን በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች አመራሮችን ለማግኘት መቻሉን እና ተማሪዎች በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ መቻሉን ገልጿል። “ከየዩኒቨርስቲዎቹ አመራሮች እና ከዓለም አቀፍ ተራድኦ ተቋማት ጋር በመሆን ጉዳዩን እየሰራንበት ይገኛል” ሲልም ጥያቄ የሚያቀርቡ ወላጆች እንዲረጋጉ መልዕክት አስተላልፏል።

በየዩኒቨርስቲዎቹ የሚገኙ ተማሪዎች የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ፈተና ለመውሰድ እየተዘጋጁ ነው ያለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ተማሪዎች ፈተና ወስደው ሲጨርሱ የሚኖሩ ጉዳዮችን እንደሚያሳውቅ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)