በሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት በኢትዮጵያ ላቋቋመው ኩባንያ ኃላፊ ሾመ

በሳፋሪኮም የሚመራው እና በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሰማራ ፍቃድ የተሰጠው ጥምረት፤ አዲስ ላቋቋመው ኩባንያ ኃላፊ ሾመ። “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” የተሰኘው ጥምረቱ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት የሾማቸው፤ በበርካታ ሀገራት በቴሌኮም ኩባንያዎች በኃላፊነት የሰሩትን አንዋር ሶሳን ነው።

የግሪክ ተወላጅ የሆኑት አንዋር ሶሳ፤ በአሁኑ ወቅት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቮዳኮም ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን በመስራት ላይ የሚገኙ ናቸው።  ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያን ጨምሮ በዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት ገበያዎች የሚገኘውን፤ በተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ማዘዋወሪያ አገልግሎትን በሊቀ-መንበርነት የሚመሩ ናቸው። 

አዲሱ ተሿሚ፤ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ትርፍ የሚዛቅበት “ቮዳካሽ (ኤም-ፔሳ)” የተሰኘውን የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ማዘዋወሪያ አገልግሎትን በበላይነት የመሩት ላለፉት አራት ዓመታት ነው። በሳፋሪኮም የሚመራው የአምስት ኩባንያዎች እና ተቋምት ጥምረት፤ ይኽንኑ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎት አለው።  

ጥምረቱ በኢትዮጵያ ገበያ ለመሰማራት የተሰጠው ፈቃድ ከአንድ ወር ገደማ በፊት በይፋዊ ስምምነት ሲጸድቅም የዚሁ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ጉዳይ ተነስቶ ነበር። በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ “የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት በኬንያ የዜጎችን ሕይወት እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሻሻል ረገድ ምን ማድረግ እንደሚችል ስለታዘብኩ፤ መንግስትዎ በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ዕድል መክፈትን ያስብበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ በስፍራው ለነበሩት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

የኬንያው ፕሬዝዳንት “ይኽ እርምጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበትን አማራጮች የሚያቀርብ በመሆኑ ወቅታዊ ነው” ሲሉ ኢትዮጵያ የአገራቸውን መንገድ እንድትከተል ገፋፍተዋል። በኢትዮጵያ በሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት የመሰማራት ፈቃድ ለጊዜው የተሰጠው ለኢትዮ-ቴሌኮም ብቻ ነው። ይህ አገልግሎት ከአንድ ዓመት በኋላ ለውድድር ክፍት እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ግንቦት ወር ጥቆማ ሰጥተዋል።

የእነ ሳፋሪኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ ስራውን ሊጀምር ያቀደው ከአምስት ወራት ገደማ በኋላ መሆኑን ማስታወቁ አይዘነጋም። ኩባንያው ወደ ስራ ሲገባ ኬንያውያን ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ “ቢዝነስ ዴይሊ” የተባለው የሀገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል። 

በኢትዮጵያ የሚቋቋመው ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና ራሱን የቻለ አስተዳደር ይኖረዋል። “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ”፤ አዲሱ ተሿሚ አንዋር ሶሳ “ጥምረቱን ወክለው የኢትዮጵያውን ኩባንያ  ይመራሉ” ሲል ትላንት ሰኞ ሰኔ 28፤ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ “በኢትዮጵያ የላቀ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት እና ከ112 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ሕይወት ለማሻሻል፤ የጥምረቱን ግብ የማስፈጸም ኃላፊነት ይጣልባቸዋል” ሲል ጥምረቱ በመግለጫው አስቀምጧል። “ጥራቱን የጠበቀ የሞባይል እና የኢንተርኔት አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ” ለኢትዮጵያ ገበያ ለማቅረብ ስትራቴጂ እና ዕቅድ የማዘጋጀት ኃላፊነትን በአንዋር ሶሳ ትከሻ ላይ የወደቀ መሆኑንም መግለጫው ጠቅሷል።

አንዋር ሶሳ ቮዳኮምን ከመቀላቀላቸው በፊት በዩጋንዳ እና በቻድ “ኤይርቴል” የተባለው የቴሌኮም ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው መስራታቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ ለመቀላቀል ከተጫረቱ ሁለት ተወዳዳሪዎች አንዱ በነበረው ኤምቲኤንም በኃላፊነት አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በካሪቢያን አገሮች የቴሌኮም ገበያ በተሰማራው ዲጂሴል በተባለ ኩባንያን በተለያዩ ኃላፊነቶች ሰርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)