በትግራይ የሰብአዊ እርዳታን በአየር ለማድረስ እስካሁን የመጣ ተቋም የለም ተባለ

በበእምነት ወንድወሰን  

በትግራይ የሚያስፈልገውን ሰብአዊ እርዳታ በአየር ለማድረስ አንድም ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት እንዳልመጣ እና እንቅስቃሴ እንዳልጀመረ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። በትግራይ ጉዳይ ላይ ትላንት ምሽት ስብሰባ ተቀምጦ የነበረው የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ በአየር ለማቅረብ “ሂዩማኒቴሪያን ኤይር ብሪጅ” የተሰኘውን አገልግሎቱን ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ዛሬ ረቡዕ ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ ለሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች ፍቃድ ቢሰጥም እስካሁን ድረስ አገልግሎቱን ፈልጎ ወደ እነርሱ የመጣ አካል የለም። የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ፤ ዛሬ በትዊተር ገጹ እንዳስታወቀው የሰብአዊ እርዳታን ለትግራይ ክልል ማቅረብ ለሚፈልጉ ሁሉም አካላት የኢትዮጵያ መንግስት የበረራ ፍቃድ የሰጠው ከሰኞ ሰኔ 28 ጀምሮ ነው። 

በረራዎቹ የሚካሄዱት አውሮፕላን ማሳረፍ ወደሚችሉ ማንኛውም የክልሉ ክፍሎች እንደሆኑ ኮለኔል ወሰንየለሁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በትግራይ ክልል ስር አራት አየር ማረፊያዎች የሚገኙ ሲሆን እነርሱም በመቐለ፣ ሽሬ እንደስላሴ፣ አክሱም እና ሁመራ ከተሞች የሚገኙ ናቸው። የሁመራ ከተማ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንዳለች መረጃዎች ያመለክታሉ።

የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች መቐለን ጨምሮ የትግራይ አካባቢዎችን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ ማቆም እርምጃን መውሰዱን ካሳወቀ በኋላ፤ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እና ሰብአዊ ድጋፍ ሰጪዎች በክልሉ ላሉ እርዳታ ፈላጊዎች ሰብአዊ አቅርቦቶችን እና ድጋፎችን ማድረስ እንዳልቻሉ ተደጋጋሚ ስሞታ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ከቅሬታ አቅራቢዎች አንዱ የሆነው የአውሮፓ ህብረት፤ በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሁለት ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው “እገዛ ለሚፈልጉ ሁሉ በቂ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ” መሆኑን ትላንት አስታውቆ ነበር። 

የአውሮፓ ህብረት ትላንት ማክሰኞ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የነበረውን ውይይት ሲያጠቃልል የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የህብረቱ ቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች “በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ በአስደጋጭ መልኩ እያሽቆለቆለ ነው” በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት አስገንዝበው ነበር። በትግራይ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች፤ መንገዶችን በመዝጋት እና ወሳኝ የሆኑ ድልድዮችን በማውደም ለሰብዓዊ አቅርቦቶች እና ለሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎች ጋሬጣ መሆናቸውንም በትላንቱ ንግግራቸው ጠቅሰዋል። 

“ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግን በማክበር፤ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ይሆን ዘንድ እንዲያስችሉ ጥሪ ማቅረባችን ሊቀጥል ይገባል” ያሉት ሌናርቺች፤ ለዚህም የአውሮፓ ህብረት በሰብዓዊም ሆነ በፖለቲካው ወገን “የበለጠ አስተዋጽኦ” ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። በሰብዓዊ አቅርቦት ረገድም፤ ህብረቱ አስቸኳይ እርዳታዎች ለማድረስ አስቸጋሪ በሆነባቸው ቦታዎች የሚጠቀምበትን “ሂዩማኒቴሪያን ኤይር ብሪጅ” የተሰኘውን አገልግሎት ለመጀመር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት “ሂዩማኒቴሪያን ኤይር ብሪጅ” የተሰኘውን አገልግሎት የጀመረው ዓለም አቀፉ የኮቪድ ወረርሽኝ መቀስቀስን ተከትሎ ነው። በግንቦት 2012 የመድሃኒት ቁሳቁሶችን ለማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በማድረስ የጀመረው አገልግሎቱ በርካታ የአፍሪካ፣ እስያ፣ የሰሜን አሜሪካ ሀገራትን አዳርሷል። አገልግሎቱ ከመድሃኒት አቅርቦት ተሻግሮ በአየር ትራንስፖርት ገደቦች እና በአስቸጋሪ የሰብዓዊ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን ቆየት ብሎ ማካተት መጀመሩን የአውሮፓ ህብረት ማብራሪያ ያሳያል።

ታጣቂ ቡድኖች በሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች ወደ ውጊያ አውድማ ለተቀየረችው የሞዛምቢኳ ካቦ ዴልጋዶ ክልል በዚህ ሳምንት እርዳታ ማድረስ የተቻለው “ሂዩማኒቴሪያን ኤይር ብሪጅ” የተሰኘውን አገልግሎት ተጠቅሞ መሆኑን የአውሮፓ ህብረት በድረ ገጹ አስነብቧል። ይህ አይነት አገልግሎት የሚሰጠው ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት እና ከእርዳታ ተቀባይ ሀገራት ጋር በሚደረግ ምክክር እንደሆነም የህብረቱ መረጃ ይጠቁሟል። 

በትግራይ ይህን አገልግሎት ለመጀመር የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነት እንደሚያስፈልግ የአውሮፓ ህብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር በትላንቱ ንግግራቸው ላይ ሳይጠቅሱ አላለፉም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሬድዋን ሁሴን ባለፈው አርብ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ለትግራይ ክልል እርዳታ ማድረስ ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ማስታወቃቸው አይዘነጋም። የእርዳታ በረራዎች በአዲስ አበባ በኩል እንደሚደረጉ እና የፌደራል መንግስትም አስፈላጊውን ክትትል እና ፍተሻ እንደሚያደርግም አስታውቀው ነበር።

“ከአዲስ አበባ ሲነሱም ሆነ ሲያርፉም በቂ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ቴክኒካል ሁኔታው ተፈትሾ መሬት ላይ ለሚሆነው ጉዳይ ግን መንግስት ኃላፊነት የሚወስድበት ጉዳይ ለጊዜው ዝግ ነው” ሲሉ የፌደራል መንግስት በቦታው ላይ ኃላፊነት እንደሌለው ገልጸው ነበር። “መቀሌ ወይም ሽሬ ሲያርፍ የሚፈጸመውን ጉዳይ በተመለከተ፤ አደጋም ቢደርስ የሚወስደው አካል ሌላ እንደሚሆን፤ መንግስት እንደማይሆን፤ ይህን አውቀውን ግን መተባበር እንደምንችል ገልጸንላቸዋል” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[ተስፋለም ወልደየስ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]