በሃሚድ አወል
የእርዳታ እህል ጭነው ወደ መቀሌ እና ሰመራ ከተሞች ሲጓዙ ነበሩ የተባሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ዘጠኝ የጭነት ተሽከርካሪዎች፤ ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ፤ ፍላቂት ገርገራ ከተማ ለሶስት ቀናት እንዲቆሙ ተደርገው የነበሩት ተሽከርካሪዎች በዛሬው ዕለት እንዲመለሱ የተደረገው በአካባቢው ያለው ህዝብ “አላሳልፍም” በማለቱ በመሆኑ ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
የመቄት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ተረፈ፤ የWFP መለያ የለጠፉ ተሽከርካሪዎች ወደ ወረዳቸው የደረሱት ከትናንት በስቲያ መሆኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ተሽከርካሪዎቹ የወረዳው ዋና ከተማ በሆነችው ፍላቂት ገርገራ እንዲቆሙ የተደረገው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሽከርካሪዎቹን “ማገት ስለፈለገ ነው” ብለዋል።
“የሚያልፈው [ተሽከርካሪ] ‘ተገቢነት የለውም የሚል ስሜት ስለነበር፤ በእኛ ጸጥታ መዋቅር ‘መኪናዎቹ ደህንነታቸው ይጠበቅ’ ብለን አስቁመን አስጠብቀናቸዋል” ሲሉ የወረዳው አስተዳዳሪ ከትላንት በስቲያ በአካባቢያቸው የተከሰተውን አስረድተዋል። “[ተሽከርካሪዎቹ] ማለፍ አይችሉም፤ ህዝቡ አያሳልፋቸውም፤ አደጋ ይደርስባቸዋል” ሲሉም በወቅቱ በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ የታየውን ስሜት ገልጸውታል።
የአካባቢው ወጣቶች በተሽከርካሪዎቹ የተጫነው እርዳታ፤ እዚያው መቄት ወረዳ ላሉ “ተፈናቃዮች ይከፋፈል” በሚል የጭነት መኪናዎቹን “አናሳልፍም” ማለታቸውን አቶ በሪሁን ተናግረዋል። በወጣቱ ዘንድ “በክልሉ የተፈናቀለ ህዝብ እያለ ለምንድን ነው ለአንድ ክልል ህዝብ ብቻ የሚረዳው? የዓለም አቀፍ ከሆነ ሁሉንም ህዝብ መመልከት አለበት የሚል በጣም የወጣ ጽንፍ አለ” ሲሉ የወረዳው አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሰሜን ወሎ ዞን ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ተጠልለው እንዳሉ አቶ በሪሁን አመልክተዋል። እርሳቸው በሚያስተዳድሩት መቄት ወረዳ ብቻ ከ2,500 በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉም አክለዋል።
በWFP ተሽከርካሪዎች የተጫነውን እርዳታ “እናውርድ” እና ለተፈናቃዮች “እናከፋፍል” ይሉ የነበሩት ወጣቶች “ኢ-መደበኛ አደረጃጀት” ያላቸው እንደሆነ የጠቀሱት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በዚህም ምክንያት የተሽከርካሪዎቹን ደህንነት ለማስጠበቅ “ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ” እንዲቆዩ መደረጋቸውን አስረድተዋል። የመቄት ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ወዳጄ መኮንን “መኪኖቹ ለራሳቸው ደህንነት ሲባል ነው እንዲቆሙ የተደረገው” ሲሉ የአስተዳዳሪውን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል።
ጥበቃ ሲደረግላቸው የነበሩት ዘጠኝ የጭነት እና ሁለት አጃቢ የWFP ተሽከርካሪዎች የተነሱት ከጎንደር መሆኑን ከያዙት ሰነድ ላይ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ኮማንደር ወዳጄ፤ መዳረሻቸውም መቀሌ እና ሰመራ እንደነበር ከሰነዱ መገንዘባቸውን ጠቁመዋል። አጃቢ የተባሉት መኪናዎች በፍላቂት ገርገራ ከተማ ሲንቀሳቀሱ እንደቆዩም ገልጸዋል።
የመቄት ወረዳ አስተዳዳሪም ሆነ የፖሊስ አዛዥ ተሽከርካሪዎቹ በፍላቂት ገርገራ ከተማ እንዲቆሙ የተደረጉት “ለራሳቸው ደህንነት ነው” ይበሉ እንጂ፤ አንድ ሌላ የወረዳው የስራ ኃላፊ ግን ከዚህ የተለየ መረጃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አጋርተዋል። የሱዳን ታርጋ የለጠፉት ተሽከርካሪዎች በወረዳው ከመድረሳቸው በፊት “ከበላይ አካል ትዕዛዝ እስኪመጣ በእናንተ ወረዳ እንዲቆዩ አድርጓቸው” የሚል ትዕዛዝ ከሰሜን ወሎ ዞን ሰላም እና ደህንነት ቢሮ እንደደረሳቸው ኃላፊው ተናግረዋል።
ተሽከርካሪዎቹን በተመለከተ ከበላይ አካል ትዕዛዝ ተላልፎላቸው እንደው የተጠየቁት፤ የወረዳው አስተዳዳሪ እና የፖሊስ አዛዥ “የደረሰን ምንም አይነት ትዕዛዝ የለም” ሲሉ አስተባብለዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የሰሜን ወሎ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያም፤ በመቄት ወረዳው ዘጠኝ የጭነት መኪናዎች ላለፉት ሶስት ቀናት ቁመው እንደነበር መረጃ እንዳላቸው፤ “ነገር ግን ከዞን የተላለፈ ምንም አይነት ትዕዛዝ አለመኖሩን” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በፍላቂት ገርገራ ከተማ የቆሙ የWFP የጭነት ተሽከርካሪዎችን ምስሎችን የሚያሳዩ እና በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ መረጃዎች፤ መኪናዎቹ ለፍተሻ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው “መታሰራቸውን” ገልጸው ነበር። ስለ ጉዳዩ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የመቄት ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ቢንያም ዘውዱ፤ “መኪናዎቹ የዓለም አቀፍ ድርጅት ንብረት ስለሆኑ ወረዳው [የመፈተሽ] mandate የለውም። ምናልባት ፌደራል ፖሊስ ካልሆነ እኛ መፈተሽ አንችልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ወዳጄም “ምንም የተፈታ ነገር የለም” ሲሉ ተሽከርካሪዎቹ በቆሙበት ወቅት ምንም አይነት ፍተሻ እንዳልተደረገባቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)