በሃሚድ አወል
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ታጣቂዎች በትላንትናው ዕለት በሰነዘሩት ጥቃት፤ ስምንት ሚሊሺያዎች እና አንድ አርሶ አደር መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ከጥቃቱ የተረፉ ሚሊሺያዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ሁለት ሚሊሺያዎች በተጨማሪነት ለቆሰሉበት ለዚህ ጥቃት የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች “ኦነግ ሸኔ”ን ተጠያቂ አድርገዋል።
የትላንቱ ጥቃት የተፈጸመው የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ አስተዳደር በጠራው ስብሰባ ላይ ተሳትፈው እየተመለሱ ባሉ ሚሊሺያዎች ላይ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። በስብሰባው ላይ ከአጋምሳ እና ሰምቦ ጨፌ የሄዱ 17 ሚሊሺያዎች መገኘታቸውን በቦታው የነበሩ አንድ ሚሊሺያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ተሰብሳቢዎቹ ተኩስ የተከፈተባቸው አመሻሽ 12 ሰዓት ገደማ ከወረዳው መሰብሰቢያ አዳራሽ ወጥተው በእግራቸው ወደ መንደራቸው እየተመለሱ በነበረበት ወቅት መሆኑን ሚሊሺያው አብራርተዋል። “ብዙም ሳንጓዝ ነው ያጠቁን” ሲሉም አክለዋል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ በንግድ ስራ የሚተዳደር የወረዳው ነዋሪ፤ “ስብሰባው በዋናነት ለሚሊሺያዎቹ የደንብ ልብስ እና ጥይት ለመስጠት ነበር። [ሚሊሺያዎቹ] በዚውም ትርዒት አሳይተዋል” ሲል የስብሰባውን ዋና ዓላማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድቷል። የወረዳው አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ኃላፊ የመሩት ስብሰባ እንደተጠናቀቀ፤ “[ወደ መንደራችን] ለመመለስ መኪና ስንጠይቅ፤ እነሱ ‘አይቻልም ሹፌሮቹ ይፈራሉ’ የሚል መልስ ነው የሰጡት” ሲል በእግራቸው የተመለሱበትን ምክንያት አስረድቷል፡፡
አቶ ሙሳ ኢብራሂም የተባሉ የአካባቢው ነዋሪም ከወረዳው የስራ ኃላፊዎች ትብብር አላገኘንም ሲሉ የሌላኛውን ነዋሪ ገለጻ አጠናክረዋል። “ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ሲደወልላቸው ‘ሰዓት መሽቷል የምንልከው አካል የለንም’ አሉን” ሲሉ ከወረዳው ኃላፊዎች ያገኙትን ምላሽ አጋርተዋል። “በሰዓቱ ቢልኳቸው ወይም ቢያሳድሯቸው ኑሮ ይኼ ሁሉ ጥቃት አይኖርም ነበር” ሲሉም ቁጭት የቀላቀለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የ55 ዓመት አርሶ አደር፤ ትላንት የተገደሉት ስምንት ሚሊሺያዎች ዛሬ ቀትር ላይ መቀበራቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በቀብሩ ቦታ ላይ ተገኝተው እንደነበር የሚናገሩት እኚሁ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከሚሊሺያዎቹ ሌላ አንድ አርሶ አደር በተባራሪ ጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉን ጠቁመዋል። የአርሶ አደሩን መገደል ሌላ የአካባቢው ነዋሪም አረጋግጠዋል።
“ህዝቡ ተማምኖ ያለው እነዚህን ሚሊሺያዎች ነበር። እነሱ ከሞቱ እኮ ዋስትና የለውም”
– በሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ነዋሪ
በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ በሚሊሺያዎች ላይ ከተሰነዘረው ጥቃት በኋላ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የደህንነት ስጋት ተቀስቅሷል። ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ በንግድ ስራ የሚተዳደር የወረዳው ነዋሪ፤ “ህዝቡ ተማምኖ ያለው እነዚህን ሚሊሺያዎች ነበር። እነሱ ከሞቱ እኮ ዋስትና የለውም” ሲል የአካባቢውን ጸጥታ በማስጠበቅ የተሰማሩት ሚሊሺያዎች መገደል የፈጠረውን ስጋት ያብራራል።
መሐመድ ኑር የተባለ የአካባቢው ነዋሪም ተመሳሳይ ስሜት አንጸባርቋል። “ለወረዳው አሉ የሚባሉ” ሚሊሻዎች መገደላቸውን የሚናገረው መሐመድ፤ ከጥቃቱ በኋላ “በጣም ፍራቻ ውስጥ ነን” ሲል ስጋቱን ገልጿል። ሌላ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የ12ኛ ክፍል ተማሪም “ጭንቀት ውስጥ ነን” ሲል የነዋሪዎችን ስጋት ተጋርቷል።
የ10 ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት 55 ዓመቱ አርሶ አደር በበኩላቸው ጥቃት አድራሾቹ በጋራ ላይ ሆነው እያዩዋቸው እንዳሉ ጠቅሰው፤ ሁኔታው “በጣም አስጊ” ነው ይላሉ። “ሴቱም ወንዱም ወደ ከተማ እየሸሸ ነው። ሚሊሺያዎች ወንድሞቻችን አለቁ። እኛም አለን ማለት አንችልም” ሲሉ በስጋት ላይ መሆናቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በጃርደጋ ጃርቴ ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የደውልንላቸው የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ “ከእናንተ ጋር ግንኑነት የለኝም። እኔ ግንኙነቴ ከዞን እና ከቀበሌ ጋር ነው” በማለት ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ እና የሆሮ ጉድሩ ዞን የጸጥታ ኃላፊዎች ግን ስለጥቃቱ “ምንም መረጃ የለንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)