ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 በጀት ዓመት 56.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

2

በሃሚድ አወል

ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 በጀት ዓመት 56.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናገሩ። በበጀት ዓመቱ የሞባይል ስልክ  የድምጽ አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር ወደ 54.3 ሚሊዮን ማደጉንም ገልጸዋል። 

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ይህን የተናገሩት የተቋሙ የ2013 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም በተመለከተ በአዲስ አበባው ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል እየሰጡት ባለው መግለጫ ላይ ነው። ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለማስገባት አቅዶ የነበረው ገቢ 55.5 ቢሊዮን ብር ነበር። ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለማስገባት አቅዶ የነበረው ገቢ 55.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር የጠቀሱት ፍሬህይወት፤ “ከዕቅዳችን በላይ 101.7 በመቶ ማሳካት ችለናል” ብለዋል።

ከአጠቃላይ ገቢው ውስጥ 47.5 በመቶ የተገኘው ከሞባይል የድምጽ አገልግሎት መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ዳታ እና ኢንተርኔት ደግሞ 27 በመቶ ያህሉን የገቢ ድርሻ መያዛቸውን አስረድተዋል። ተቋሙ በየጊዜው ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ተቋሙ ከዕቅዱ በላይ ገቢ እንዲያስገባ እንዳስቻለውም ጠቁመዋል። 

ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በመላ አገሪቱ የኢንተርኔት መቋረጥ በመከሰቱም ተቋሙ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ ማጣቱንም ገልጸዋል። “ክስተቱ የ2013 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ መከሰቱ ያልጠበቅነው ነበር” ሲሉም ፍሬህይወት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  

በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ የ48.2 በመቶ የደንበኞች እድገት መመዝገቡን አስታውቋል። በሐምሌ 2010 የነበረው የ37.92 ሚሊዮን የቴሌኮም ተጠቃሚ ቁጥር፤ በሰኔ 2013 ወደ 56.2 ሚሊዮን ማደጉም በዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል። ኢትዮ ቴሌኮም ከ2010 ጀምሮ ያደረገው ማስፋፊያ የተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል። 

የሞባይል ድምጽ ተጠቃሚዎች ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረበት 36.37 ሚሊዮን ወደ 54.3 ሚሊዮን ማደጉን የገለጹት ፍሬህይወት፤ ይህም የ49.3 በመቶ ጭማሪ መሆኑን ጠቁመዋል። በሞባይል ዳታ ተጠቃሚዎች ረገድም የ40 በመቶ እድገት መታየቱንም አንስተዋል። የዛሬ ዓመት 17. 81 ሚሊዮን የነበሩት የሞባይል ዳታ ተጠቃሚዎች አሁን 25 ሚሊዮን መድረሳቸውን አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)