ኢዜማ በ28 ምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫው እንዲደገም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማስገባቱን አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሰኔ 14፤ 2013 ምርጫ ከተካሄደባቸው ምርጫ ክልሎች ውስጥ የሃያ ስምንቱ ምርጫ እንዲደገም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማስገባቱን አስታወቀ። ፓርቲው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እነዚህን ምርጫ ክልሎች በተመለከተ የቀረቡለትን “ቅሬታዎች እና ማስረጃዎች ሳይገመግም ውሳኔ በማስተላለፉ” ነው ብሏል።    

የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ፓርቲው ምርጫው እንዲደገም አቤቱታ ያቀረበባቸው ሁሉም ምርጫ ክልሎች በደቡብ ክልል የሚገኙ ናቸው። አቤቱታ ከቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ ሃያ አራቱ፤ ፓርቲው ለፓርላማ እና ለደቡብ ክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ዕጩዎች ያቀረበባቸው እንደሆኑ ገልጸዋል። በቀሪዎቹ አራት የምርጫ ክልሎች ደግሞ የክልል ምክር ቤት ምርጫ ብቻ የተካሄደባቸው መሆናቸውን አክለዋል። 

ፓርቲው በእነዚህ የምርጫ ክልሎች ላይ ያለውን አቤቱታ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስገባው ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 14 መሆኑን ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አቤቱታውን የተቀበለው ፍርድ ቤቱ፤ ከነገ ሐሙስ ሐምሌ 15 ጀምሮ ጉዳዩን መመልከት እንደሚጀምርም መግለጫው ጠቁሟል።  

ኢዜማ ለፍርድ ቤቱ ያስገባው አቤቱታ “ከበቂ በላይ ማስረጃ” አቅርቤባችኋለሁ ያላቸውን 28 የምርጫ ክልሎች የተመለከተ ይሁን እንጂ፤ ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ ያቀረበባቸው አጠቃላይ የምርጫ ክልሎች ብዛት 68 ናቸው። ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ከተካሄደ ከአራት ቀናት በኋላ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው የፓርቲው አቤቱታ፤ የሰው፣ የሰነድ፣ የቪድዮ እና የምስል ማስረጃዎችን ያካተተ እንደሆነ በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል። 

ኢዜማ በዚሁ ቅሬታው “በድምጽ አሰጣጥ ሂደት እና በምርጫ ውጤት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ ተግባራት መፈጸማቸውን” ለቦርዱ አቅርቧል ተብሏል። ተግባራቱ “የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን፣ የምርጫ አዋጅን እና ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን መመሪያዎች በቀጥታ የሚጻረሩ” መሆናቸውን ፓርቲው ጠቅሷል። 

የዛሬው የኢዜማ መግለጫ እነዚህን ተግባራት በመፈጸመ የተወነጀሉ አካላትንም ዘርዝሯል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ የገዢው ፓርቲ አመራሮች፣ ከቀበሌ ሚሊሺያ እስከ ክልል ልዩ ኃይል ድረስ ያሉ የጸጥታ አስከባሪዎች፣ የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና ለጊዜው ማንነታቸውና ሕጋዊ የሥራ ኃላፊነታቸው በግልጽ ያልታወቀ ግለሰቦች ተካትተዋል።

ኢዜማ ቅሬታ ያቀረበባቸውን የምርጫ ክልሎች በተመለከተ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)