በሃሚድ አወል
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩት ኮማንደር ፈረዴ ቦጅ ዛሬ ሐሙስ ጠዋት በታጣቂዎች መገደላቸውን የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ የተገደሉት በካማሺ ዞን ወደምትገኘው ሴዳል ወረዳ በመጓዝ ላይ ባሉበት ወቅት ነበር ተብሏል።
የካማሺ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ቦካ አቦሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ በኮማንደር ፈረዴ እና አብረዋቸው በነበሩ ሁለት ሰዎች ላይ ጥቃት የተፈጸመው በአሶሳ ዞን በሚገኘው እና ሴዳል ወረዳን በሚያዋስነው ኦዳ ብልጉዱል ወረዳ ነው። በጥቃቱ ኮማንደር ፈረዴን ጨምሮ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን እና የሁለቱ ግለሰቦች ማንነት ግን ለጊዜው አለመታወቁን አስረድተዋል።
የጥቃቱ ፈጻሚዎች እነማን እንደሆኑ በግልጽ አለመታወቁን የሚናገሩት የካማሺ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፤ “ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ የጸጥታ አካላት ገና እያጣሩት ነው” ብለዋል።
የሴዳል ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጨምር ሁንዴሳም፤ የቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ በዛሬው ዕለት በታጣቂዎች መገደላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ኮማንደር ፈረዴ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው የትውልድ አካባቢያቸው ወደሆነው ሴዳል ወረዳ በመጓዝ ላይ ባሉበት ወቅት እንደነበርም ገልጸዋል።
ከኮማንደር ፈረዴ ጋር የቅርብ ትውውቅ እንዳላቸው የተናገሩ አንድ የሴዳል ወረዳ ነዋሪ፤ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስን ስለመቀላቀላቸው ተናግረዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እኚሁ ነዋሪ ኮማንደሩ ከ2005 ጀምሮ የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ሆነው እስከ 2011 ማብቂያ ድረስ ማገልገላቸውን ገልጸዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በ2011 ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት “እጃቸው አለበት” በሚል ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውንም ነዋሪው አስታውሰዋል። ኮማንደሩ ከኃላፊነት ከተነሱበት ወቅት ጀምሮ የወር ደመወዛቸው ሳይቋረጥ በቁም እስር ላይ መቆየታቸውንም አክለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ዛሬ የተሰራጩ መረጃዎች ግን የቀድሞው የልዩ ኃይል አዛዥ ዛሬ ጠዋት ጥቃት የተፈጸመባቸው፤ መንግስትን ወክለው በአካባቢው ካሉ አማጽያን ጋር ለመደራደር በሄዱበት ቦታ እንደሆነ ጠቁመዋል። ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት የአካባቢው ባለስልጣናት ስለ ተባለው ነገር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። የጥቃቱ ፈጻሚዎች እነማን እንደሆኑ እስካሁን በግልጽ አለመታወቁንም ጨምረው ገልጸዋል።
የካማሺ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ “ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ የጸጥታ አካላት ገና እያጣሩት ነው” ሲሉ አቶ ቦካ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የዛሬውን ጥቃት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም ከክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)