በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ላይ በፍርድ ቤት ክስ ተመሰረተ

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ የተካተቱ 62 ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ክስ መመስረቱን ዛሬ አርብ ሐምሌ 16፤ 2013 አስታውቋል። ተከሳሾቹ በሕገ መንግስትና በሕገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀልን እንዲሁም የሽብርተኝነት ድርጊቶች በመፈጸም መከሰሳቸውንም ገልጿል። 

ተከሳሾቹ ላይ ከቀረቡባቸው ሁለት ክሶች ውስጥ አንደኛው በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ፣ ኢ-ሕገመንግስታዊ ምርጫ በማካሄድ፣ በሕገ-መንግስት የተቋቋመና እውቅና ያለውን የክልል መንግስት የመለወጥ ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው። እነ ዶ/ር ደብረጽዮን በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከዕድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በወንጀል ህጉ ላይ ተቀምጧል።

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ የተመሰረተው ሁለተኛው ክስም፤ ከ15 ዓመት እስራት ጀምሮ እስከ ሞት የሚደርስ ተመሳሳይ ቅጣት ያዘለ ነው። ይህ ክስ፤ ስልሳ ሁለቱ ተከሳሾች የፌዴራሉን መንግስት በኃይል ለመለወጥ በማሰብ፣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የፌዴራል መንግስትን በመሳሪያ ጥቃት መለወጥ የሚችል የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ የተባለ የጦር ሀይል በማደራጀት፣ በፌዴራል መንግስት የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጥቃት አድርሰዋል በሚል የቀረበ ነው። 

ዐቃቤ ሕግ እነዚህን ክሶች ያስረዱልኛል ያላቸውን 510 የሰው ምስክሮችን እና እና 5,329 የገጽ ብዛት ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎችን በማያያዝ ለፍርድ ቤት አቅርቤያለሁ ብሏል። ክሶቹን የሚመለከተው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸረ- ሽብር እና ሕገ-መንግስት ጉዳዮች 1ኛ ችሎት መሆኑም ተነግሯል። 

ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተከሳሾች ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ለሐምሌ 26፤ 2013 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዛሬ ባወጣው መረጃ አመልክቷል። በዚህ መዝገብ የተካተቱ አብዛኞቹ ተከሳሾች በሌሉበት የተከሰሱ ሲሆን፤ የፌደራል ፖሊስ ለእነዚሁ ተከሳሾች መጥሪያ በማድረስ በተመሳሳይ ቀጠሮ በአካል እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱንም ጨምሮ ገልጿል።

ዛሬ ክስ ከተመሰረተባቸው ግለሰቦች ውስጥ ስምንቱ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ናቸው። ዐቃቤ ህግ “ውሳኔ በመስጠት ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው” ያላቸው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በክሱ ተካትተዋል። የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩ ታዋቂ ግለሰቦችም እንዲሁ የክሱ አካል ሆነዋል። 

የትግራይ ክልል መንግስት የካቢኔ አባላት የነበሩ እንዲሁም የመንግስት፣ የኤፈርት እና የግል ድርጅቶች አመራሮች ከተከሰሱት ውስጥ ይገኙበታል። የፌደራል መንግስት “ኢ-ሕገ-መንግስታዊ” ሲል ውድቅ ያደረገውን የትግራይ ክልልን ምርጫ ያስፈጸሙ የምርጫ ኮሚሽን አመራር አባላት እና በምርጫው ላይ ተሳትፎ ያደረጉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊቃነ-መናብርትም በተከሳሾች ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ተገልጿል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)